ሙሉአለም ጥላሁን ወደ ኬንያ ሊያመራ ይችላል

የመከላከያው አጥቂ ሙሉአለም ጥላሁን በናይሮቢው ክለብ ኤኤፍሲ ሊዎፓርድስ እየታደነ መሆኑን ፉታ ድረገፅ ዘግቧል። ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር በፈጠረው ውዝግብ ምክኒያት በውድድር ዓመቱ አጋማሽ በ275,000 ብር ክፍያ ለ6 ወራት መከላከያን የተቀላቀለው ሙሉአለም ቀጣይ ማረፊያው አልታወቀም።

የቀድሞው የመድን እና ኢትዮጵያ ቡና አጥቂ መከላከያ ከኬንያው ክለብ ጋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እና በሱዳን በተዘጋጀው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ክለቦች ዋንጫ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተሰልፎ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። የተጫዋቹ ወኪልም በቅርቡ ወደ ናይሮቢ በመሄድ ከክለቡ ጋር ለድርድር እንደሚቀመጥ ተነግሯል።

“ሙሉአለም ጥሩ ብቃት ያለው ተጫዋች ነው፤ በቋሚነት ለክለባችን እንዲፈርምም እንፈልጋለን። ደጋፊዎቻችንም የተጫዋቹን ችሎታ ሲመለከቱ እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ነኝ፤” ሲሉ የሊዎፓርድስ ክለብ ባለስልጣን ተናግረዋል።

በኬንያ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚከፈላቸው ዝቅተኛ የሆነ ገንዘብ ግን ዝውውሩን እንዳያደናቅፈው ተሰግቷል። በህዳር ወር የወጣ አንድ ጥናት ማይክ ባራዛ የተባለው የዚያው የሊዎፓርድስ ክለብ አጥቂ በወር 85 ሺህ ሽሊንግ ወይም 970 ዶላር በማግኘት የሊጉ ከፍተኛ ተጫዋች እንደሆነ ገልፆ ነበር። ሙሉአለም ጥላሁን በሀገር ውስጥ ማግኘት ከሚችለው የተሻለ ገንዘብ ካልቀረበለት የኬንያውን ክለብ ይቀላቀላል ተብሎ አይጠበቅም።

ሊዎፓርድስ እ.ኤ.አ. በ1964 ዓ.ም. የተቋቋመ ክለብ ሲሆን በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች 30,000 ተመልካቾች በሚይዘው ንያዮ ስታዲየም ያስተናግዳል። በኬንያ ከሚገኙ 2ቱ ትልቅ ክለቦች አንዱ የሆነው ሊዎፓርድስ በሆላንዳዊው አሠልጣኝ ፒተር ሄንድሪክ ዴ ጆንግ ይሠለጥናል፣ በአሁኑ ጊዜም በኬንያ ፕሪምየር ሊግ 2ተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል።

 

ያጋሩ