የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው እለት 4 ጨዋታዎች በመሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታድየም ተካሂደው ወደ አንደኛ ሊግ የገቡ የመጀመርያዎቹ 4 ክለቦች ተለይተዋል፡፡ ሺንሺቾ ከተማ ፣ ሰንዳፋ በኬ ፣ ድሬዳዋ ኮተን እና ናኖ ሁርቡ ወደ አንደኛ ሊግ ማደጋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው፡፡
በረፋድ 03:00 መረሀ ግብር የተገናኙት ሺንሺቶ ከተማ እና በአረካ ከተማ ቅጣት ምክንያት ከምድቡ ማለፍ የቻለው ነስር ክለብ ነበሩ፡፡ ሺንሺቾ ከተማም 2-1 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊጉ ያደገ የመጀመርያው ክለብ ሆኗል፡፡
በሜዳው ላይ በተገኙ ጥቂት የሺንሺቾ ደጋፊዎች ህብረዝማሬ ሞቅ ብሎ በጀመረው ጨዋታ ተጭነው የተጫወቱት ሺንሺቾዎች በ7ኛው ደቂቃ ከቅጥት ምት የተሻማውን ኳስ በሚሊዮን ካሳ አማካኝነት አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ ንስር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ሺንሺቾ በመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውሏል።
ከእረፍት መልስ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ነስሮች ቢሆኑም ግን ግብ ማስቆጠር የቻሉት ሺንሺቾዎች ነበሩ፡፡ በ66ኛው ደቂቃ አካሉ ተፈራ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ በማራኪ ሁኔታ መትቶ ከመረብ ጋር በማዋሀድ የሺንሺቾን መሪነት ወደ 2 ከፍ አድርጓል፡፡ ከ2 ደቂቃ በኋላ ከቀኝ መስመር ወደ ጎል የተሻገረውን ኳስ የነስሩ ኸድር የሱፍ በግምባር ገጭቶ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በሺንሺቾ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ቀጥሎ 05:00 ላይ የተካሄደው የሰንዳፋ በኬ እና ጫንጮ ከተማ ጨዋታ በሳቢ እና ፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ በሰንዳፋ በኬ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ሰንዳፋዎች በ29ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በከድር ናስር አማካኝነት አስቆጥረው ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ለእረፍት ሰከንዶች ሲቀሩ ጫንጮ በዋለልኝ አያሌው አማካኝነት ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም በሰንዳፋው ግብ ጠባቂ ኤርሚያስ አሰፋ ከሽፏል።
ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ፈጣን እና ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች የተስተዋሉ ሲሆን አላስፈላጊ እልህ መጋባቶች ተስተውለዋል።
በ86 ደቂቃም የሰንዳፋው ግብ ጠባቂ በፈጠረው ስህተት ጫንጮ ወርቃማ የግብ እድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው በሰንዳፋ በኬ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
08:00 ላይ በተደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ኮተን ከኦሮሚያ ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2-2 ተለያይተው በተሰጡ የመለያ ምቶች ኮተን 4-2 አሸንፎ ወደ አንደኛ ሊግ ማደግ ችሏል፡፡ በ1992 ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከወረደ በኋላ ፈርሶ የነበረው የ5 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ (ኮተን) ለማስታወስ በ2007 በአካባቢው በጎ ፈቃደኞች ተመስረቶ ዘንድሮ ለአንደኛ ሊግ በቅቷል፡፡
በእለቱ የመጨረሻ መርሀግብር ገንፈል ውቅሮን የገጠመው ናኖ ሁርቡ 2-0 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊጉ ማደግ የቻለ አራተኛው ክለብ መሆን ችሏል፡፡
የውድድሩ ሁለተኛ ዙር ቀጣይ ጨዋታዎች በነገው እለት ተካሂደው ወደ አንደኛ ሊጉ የሚያልፉ ተጨማሪ 8 ክለቦች የሚለዩ ይሆናል፡፡
[table id=381 /]