ኬንያዎች ውጤቱን መቀልበስ እንደሚችሉ እየተናገሩ ነው

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የኬንያ አቻውን 2-0 አሸንፎ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ለማለፍ የሚያስችውን እድል አስፍቶ ወደ ናይሮቢ አምርቷል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም አጥቅተው በመጫወት ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት እንደተዘጋጁ ትላት ናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀራምቤ ከዋክብት ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ እድላቸው እንዳልተሟጠጠ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

 

የሊዮፓርድሱ ቤርናርድ ማንጎሊ ለሱፐር ስፖርት በሰጠው አስተያየት ጨዋታው ገና እንዳልተጠናቀቀ ተናግሯል፡፡ ‹‹ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያሳልፈንን ውጤት ማግኘት እንደምንችል እተማመናለሁ፡፡ ›› ሲል ሀሳቡን መስጠት የጀመረው ቤርናርድ ውጤቱን መቀበስ ከባድ ቢሆንም የማይቻል እንደሆነ ያምናል፡፡

‹‹ 2-0 መሸነፍ ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር፡፡ በጨዋታው የፈጠርናቸው የግብ እድሎችንም ወደ ግብ መቀየር አልቻልንም፡፡ ››

‹‹ በናይሮቢ 90 ደቂቃ ይቀረናል፡፡ እድላችንን ለመወሰን ሜዳ ላይ ያለንን ሁሉ መስጠት አለብን፡፡ ጨዋታው እንዳልተጠናቀቀ በማሰብ መልካም አቋም አሳይተን የምንፈልገውን ውጤት ማሳካት እንችላለን›› ሲል በባህርዳሩ ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊ የነበረው ቤርናርድ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

አሰልጣኙ ቦቢ ዊልያምሰን ለዴይሊ ኔሽን በሰጡት ቃል ደግሞ በደጋፊያቸው ፊት ውጤቱን ቀልብሰው ወደ ተከታዩ ዙር እንደሚያልፉ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹ በጨዋታው የሚያስፈልገን አንድ ግብ ብቻ አይደለም፡፡ ሶስት ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅብናል፡፡ ይህን በደጋፊያችን ፊት እንደምናሳካም ተስፋ አለኝ፡፡ነገር ግን በ2-0 ሽንፈት የመልስ ጨዋታ ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ›› ሲሉ ለማሳካት ከባድ ቢሆንም ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ ተስፋቸው እንዳልመነመነ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡

 

ያጋሩ