ቻን 2018: ዋልያዎቹ ለነገው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል

በ2018 በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ለማለፍ የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር ነገ 10:00 ላይ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረፋድ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

አሰልጣኝ አሸናፊ ከዛምብያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ መልስ ከስብስባቸው የፋሲል ከተማውን የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን በመቀነስ በምትኩ ተካልኝ ደጀኔን ከአርባምንጭ ሲጠሩ በተጨማሪ ታደለ መንገሻ ከቡድኑ ጋር አካተው ያለፉትን ስድስት ቀናት ( ሦስቱን ቀናት በቀን ሁለቴ ልምምድ በመስራት) ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው ከሐሙስ ዕለት ጀምር እስከ ዛሬ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዳቸው ድረስ በቀን አንድ ጊዜ ሰርተዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ የነበረው የመጨረሻ ልምምዳቸው ለአንድ ሰአት ያህል ቆይታ ሲኖረው በልምምዳቸው ወቅት የቡድኑን መንፈስ ሊያነቃቁ የሚችሉ በቡድን ተከፍለው አዝናኝ የሆነ ጨዋታ በመጫወት የጀመረው ልምምዳቸው በመቀጠል ቀለል ያሉ ኳስን መሰረት ያደረገ በሁለት ተከፍለው በፈጣን እንቅስቃሴ የጎል እድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ልምምድ አድርገዋል። በልምምድ ወቅት በአሰልጣኞቹም ሆነ በተጨዋቾቹ በኩል በአንድነት መንፈስ ለነገው ጨዋታ ከፍተኛ የሆነ የተነሳሽነት ስሜት ሲሰሩ ለመመልከት ችለናል።

ከሰኞ ጀምሮ በነበራቸው የዝግጅት ቆይታ በጉዳት ጋር ተያይዞ ከነገው ጨዋታ ከቡድኑ ውጪ የሆነው ታደለ መንገሻ ሲሆን የተቀሩት ሁሉም ተጨዋቾች ለነገው ወሳኝ ጨዋታ በሙሉ ጤንነት ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል።

ከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ቡድኑ በአንድነት መንፈስ በመሆን ለጨዋታው ዝግጁ እንዲሆን የማነቃቂያ ንግግር ካደረጉ በኋላ ቡድኑ ሱዳንን ካሸነፈ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከትለት ተናግረዋል ።

የነገውን ወሳኝ ጨዋታ በዳኝነት የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከኡጋንዳ ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ከግብፅ ናቸው። የኢትዮዽያ ከሱዳን የሚያደርጉት ጨዋታ ነገ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስቴዲዮም ከቀኑ 10:00 ሲካሄድ የስቴዲዮም መግቢያ ትኬት ከ20 እስከ 10 ብቻ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡

በመጨረሻም
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከቀናት ዝምታ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የጋዜጣዊ መግለጫውን አጠቃላይ ሀሳብ ከሰአታት በኋላ ይዘን የምንቀርብ መሆናችንን እንገልፃለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *