ለአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ለማለፍ በምስራቅ እና መካከለኛው ዞን ሀዋሳ ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ሱዳን 1-1 ተለያይተዋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ላይ ለሚኖረው የመልስ ጨዋታ የሱዳን ብሄራዊ ቡደን ተጠቃሚ የሚያደርገውን ውጤት ከኢትዮጵያ ላይ መውሰድ ችሏል፡፡ የተቀዛቀዘ የመጀመሪያ አጋማሽ፣ የዋሊያዎቹ ደካማ የጨዋታ እንቅስቃሴ እንዲሁም የእንግዶቹ የሁለተኛ አጋማሽ የሙከራ ብልጫ እና የጀማል ጣሰው ድንቅ ብቃት የጨዋታው አጠቃላይ መገለጫዎች ነበሩ፡፡
በመጀመሪያው 45 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፈጣን ቅብብል የሱዳን ብሄራዊ ቡድንን ጫና ውስጥ ለመክተት ያለመ እንቅስቃሴ ቢያደርግም የእንግዶቹ የተደራጀ የመከላከል ብቃት ዋሊያዎቹን እምብዛም ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል እንዲደርሱ አላስቻላቸውም፡፡ ዋሊያዎቹ በተደጋጋሚ የሱዳንን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በአጭሩ የሜዳው የመሃል ክፍል ላይ ነበር ተቆርጦ የሚቀረው፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ በ18ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ የሱዳን ተከላካይ አብደራህማን ኢሳግ በስህተት ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው አክራም ኤልሃዲ ሳሊም አምክኖበታል፡፡ እንግዶቹ ከ22-30ኛው ደቂቃ ባለው ግዜ በኢሳግ፣ ሰይፈልዲን ማኪ፣ አብደልራህማን መአዝ እና ዝነኛው የሱዳን አጥቂ መሃመድ ጣሂር ኦስማን አማካኝነት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ከርቀት ከመሞከራቸው ውጪ ሁለቱም ቡድኖች በሚቆራረጥ የጨዋታ ፍሰት ጨዋታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በ34ኛው ደቂቃ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ግብ ቢሞክርም አክራም አምክኖበታል፡፡ በተቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ኢላማቸውን የጠበቁ እና ግብ ጠባቂዎችን ሊፈትኑ የሚችሉ ኳሶችን እምብዛም ሲያገኙ አልተስተዋለም፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ቢገቡም ቡድኑ ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ መልኩ እጅግ በጣም ተዳክሞ ቀርቧል፡፡ ምንተስኖት አዳነ እና ብሩክ ቃልቦሬ ታፈሰ ሰለሞንን እና አብዱልከሪም መሃመድን ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በቡድኑ ውስጥ የሚገኘው ብቸኛው የቀኝ መስመር ተከላካይ አብዱልከሪም ተቀይሮ መውጣቱን ተከትሎ የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ የቀኝ መስመር ተከላካይ ለመሆን ተገዷል፡፡ የሱዳኑ አሰልጣኝ መሃመድ አብደላ አህመድ (ማዝዳ) ፈጣን የሆኑት የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ተጠቅመው ወደ ግብ መቅረብ እንደሚችሉ ማመናቸው በሁለተኛው 45 ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ማኪ ከጀማል ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሃገሩን ቀዳሚ ማድረግ የሚችልበትን ወርቃማ እድል ሲያመክን ከ57-59 ባሉት ደቂቃዎች ደግሞ ጀማል በድንቅ ሁኔታ ሁለት ኳሶች ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡ በ57ኛው ደቂቃ አቡአግላ አብደላ በቮሊ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የመታውን ጠንካራ ኳስ ጀማል በድንቅ ሁኔታ ሲያመክን ከደቂቃ በኃላ የማኪን የግንባር ኳስም ከግብነት ታድጓል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ኳሶችን በረጅሙ ወደፊት ለመጣል ቢሞክርም ይህ አጨዋወት ሱዳኖች ይበልጥ በነፃነት እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል፡፡ በ76ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ማኪ ብቻውን እየገፋ ሄዶ የኢትዮጵያ መረብ ላይ አሳርፎ በስታዲየሙ የተገኙ ጥቂት የሱዳን ደጋፊዎችን አስፈንድቋል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላም እንግዶቹ በራስ መተማመናቸውን አድጎ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ሲያጠናክሩ ባለሜዳዎቹ ግራ ተጋብተው ታይተዋል፡፡
በ83ኛው ደቂቃ ዋለልዲን ከድር ዳየን ወደ ግብ የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚን ታኮ ወደ ውጪ ሲወጣበት ከደቂቃ በኃላ ኤልሳማኒ ኤልሳዊ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ከኢትዮጵያ በኩል ጥሩ የነበረው ጀማል መልሶበታል፡፡ የተመለሰው ኳስ በረጅሙ ወደ ሱዳን የግብ ክልል የተላከውን ኳስ አብዱልራህማን ሙባረክ አግኝቶ በአክራም አናት ላይ በማስቆጠር ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል፡፡ አብዱልራህማን የሱዳን ተከላካዮች የሰሩትን ጨዋታ ውጪ አቋቋም በማክሸፍ ነው በነጥብ ጨዋታ የመጀመሪያ ግቡን ለዋሊያዎቹ ማስቆጠር የቻለው፡፡ የአቻነት ግቡ ከተቆጠረ በኃላም በስታዲየም የተኘው ደጋፊ ዋሊያዎቹ ተጨማሪ ግብ እንዲያስቆጥሩ ማበረታታት ጀምሯል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ግቦች ሳይቆጠሩ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ሱዳን የመልስ ጨዋታ በመጪው አርብ ኦቢየድ ላይ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ በ2014 እና 2016 የቻን ውድድሮች ተሳትፎ ስታደርግ በ2011 ውድድሩን ያዘጋጀችው ሱዳን ለቻን ውድድር ካለፈች 6 አመታት ተቆጥረዋል፡፡