የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በጉለሌ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ማክሰኞ በተዴገ የፍጻሜ ጨዋታ ሲጠናቀቅ ጉለሌ ክፍለከተማ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ 30 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ የተጀመረውና በአቃቂ እና ናኖ ሁርቡ መካከል የተደረገው የደረጃ ጨዋታ ጥሩ የሚባል ፍክክር ተስተውሎበት በአቃቂ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ21ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ አስማረ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት በማራኪ ሁኔታ አስቆጥሮ አቃቂ ቃሊቲን ቀዳሚ ማድረግ ሲችል 45ኛው ደቂቃ ፀጋዬ በኃይሉ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መትቶ የአቃቂን መሪነት ማስፋት የሚችልበትን እድል ቢያመክንም በ57ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ አስቆጥሮ የአቃቂ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላም ወደ ግብ ክልላቸው የተላከውን ኳስ ናኖ ሁርቡዎች በአግባቡ ማራቅ ባለመቻላቸው አቃቂዎች ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መገባደድ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥሩ የሆነ ስፖርታዊ ጨዋነት የተመለከትን ሲሆን አቃቂዎች በሜዳ የተገኘውን ደጋፊ ተዟዙረው በማመስገን እና ለፍፃሜ ያለፍትን ቡድኖች ግራ እና ቀኝ በመሆን በጭብጨባ ተቀብለው ተሰናብተዋል።

ቀጥሎ በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንደግዶች ተጫዋቾችን በመተዋወቅ ጨዋታውን አስጀምረዋል።

በርከት ብለው በተገኙት የሰንዳፋ በኬ ደጋፊዎች ድጋፍ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጉለሌዎች በተደጋጋሚ የሰንዳፋ ግብ ክልልን ፈትሸዋል። የጨዋታው ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ሁለቱም ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በእረፍት ሰአት ለውድድሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱት ቀይ መስቀል ፣ የወልድያ ከተማ ጤና ጣቢያ ፣ የፀጥታ አካላት (የአማራ ክልል አድማ በታኝ ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ ፣ የወልድያ ከተማ ፖሊስ) እንዲሁም ሌሎች አካላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ከእረፍት መልስ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል እንደመጀመሪያው አጋማሽ ቢስተዋልም ግልፅ የሆነ የግብ እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም በመጨረሻ በ88ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በኩል አሸናፊ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የሰንዳፋው አምበል ሀሰን ሙሀመድ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ ጉለሌ ባለድል መሆን ችሏል፡፡

ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ለአሸናፊዎች እና ኮከቦች ሽልማት ተበርክቷል፡፡

3ኛ. አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ – 10,000 ብር
2ኛ. ሰንዳፋ በኬ – 20,000 ብር
1ኛ. ጉለሌ ክፍለከተማ – ዋንጫ እና 30,000 ብር

ኮከብ ተጫዋች – በረከት አምባዬ (ጉለሌ)
ከፍተኛ ግብ አግቢ – ሳሙኤል ዘሪሁን (ድሬዳዋ ኮተን)
ኮከብ አሰልጣኝ – ይልቃል (ጉለሌ)
ምስጉን ዋና ዳኛ – አህመድ ሲራጅ
ምስጉን ረዳት ዳኛ – ታምሩ አደም
ለመልካም መስተንግዶ – ወልድያ ከተማ አስተዳደር (ዋንጫ)
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ – ናኖ ሁሩቡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *