ቢኒያም በላይ ተጠባባቂ በነበረበት ጨዋታ ስኬንደርቡ ወሳኝ ውጤት አግኝቷል

ወደ ዩሮፓ ሊግ የምድብ ድልድል ለመግባት ጥረት እያደረገ የሚገኘው የአልባኒያው ስኬንደርቡ ኮርሲ ከሜዳው ውጪ ዛግሬብ ላይ ከክሮሺያው ኃያል ዳይናሞ ዛግሬብ ጋር ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በአልባኒያው ክለብ ለመጫወት የሶስት አመት ውል የፈረመው ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይም ጨዋታውን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ተመልክቷል፡፡ የኮርሲ ከተማ ክለብ የሆነው ስኬንደርቡም ለቢኒያም የ18 ቁጥር መለያ ሰጥቶታል፡፡

እንግዶቹ ከዛግሬብ ያልተጠበቀ ውጤትን ይዘው ሲመለሱ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ሊሪዶን ላቲፊ በ37ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ዳይናሞ ዛግሬብ ከቺሊያዊው አንሄሎ ሄኔሪኬዝ ግብ 1-1 ጨዋታውን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ የመልስ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ሃሙስ ሲካሄድ ስኬንደርቡ የማለፍ ተስፋውን ከወዲሁ አስፍቷል፡፡ ቢኒያም በጨዋታውን ላይ መሰለፍ ባይችልም በተጠባባቂነት ተይዞ ጨዋታውን ተመልክቷል፡፡



ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በአውሮፓ የክለብ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ ባይታይም ከዚህ ቀደም ለሌላ ሀገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በአውሮፓ የክለብ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ ተመልክተናል፡፡ በጎንደር የተወለደው ቤተ-እስራኤላዊው ብሩክ ደጉ በአውሮፓ ውድድሮች ስኬታማ ከሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚው ነው፡፡ ብሩክ ማካቢ ቴልአቪቭ በ2004/05 የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ግርጌ ላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በታላላቆቹ ጁቬንቱስ ፣ ባየርን ሙኒክ እና አያክስ አምስተርዳም መረብ ላይ 4 ጎሎች ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡

ቋራ የተወለደውና እነደ ብሩክ ሁሉ ቤተ-እስራኤላዊ የሆነው አማካዩ ስንታየሁ ሳሊቺ ሌላው ተጠቃሽ ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞ የማካባ ሃይፋ እና ቤይታር ጀሩሳሌም ኮከብ በ2014 ከስሎቬኒያው ኤንኬ ማሪቦር ጋር በዩኤፋ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በተመሳሳይ አመት ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰብ የተገኘው ጌዲዮን ዘላለም በአርሰናል መለያ ጋላታሳሪያን በቻምፒየንስ ሊግ መግጠሙ ይታወሳል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ቢኒያም ለስኬንደርቡ መጫወት ከቻለ በአውሮፓ ክለቦች መድረክ የተጫወተ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *