ባምላክ ተሰማ የቻን እና የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እንዲመራ ተመርጧል

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) እና አለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እንዲመራ ተመርጧል፡፡ ባምላክ የቻን ማጣሪያ ሹመቱን ያገኘው ከካፍ ሲሆን የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ሹመቱን ደግሞ ከፈፋ ነው፡፡

በቻን ማጣሪያ በደቡብ ዞን ሉዋንዳ ላይ አንጎላ ከማዳጋስካር የሚያደርጉትን ጨዋታ ባምላክ በመሃል ዳኛነት ይመራል፡፡ የባምላክ ረዳት በመሆን የኢስታዲዮ 11 ኖቨምበርን ጨዋታ የሚመሩት ደግሞ ክንፈ ይልማ፣ ሸዋንግዛው ተባባል እና ብሩክ የማነብርሃን ናቸው፡፡ ጨዋታው ቅዳሜ የሚደረግ ሲሆን ከሳምንት በፊት አንታናናሪቮ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሃገራቱ ያለምንም ግብ አቻ መለያየታቸው ይታወቃል፡፡

ባምላክ በሩሲያ በ2018 ለምታስተናግደው የአለም ዋንጫ ለማለፍ ሊቨርቢል ላይ ጋቦን ከኮትዲቯር የሚያደርጉትን ጨዋታ ይመራል፡፡ ቅዳሜ ነሃሴ 27 በሚደረገው የምድብ ሶስት ወሳኝ ጨዋታ የባምላክ ረዳት የሆኑት ኦሊቨር ሳፋሪ ካቤና ከዲ.ሪ. ኮንጎ እንዲሁም ማርክ ሶንኮ ከዩጋንዳ ሲሆኑ አራተኛ ዳኛ የሆነው ኢትዮጵያዊው ሃይለየሱስ ባዘዘው ነው፡፡ ዩጋንዳዊው ማርክ ሶንኮ ኢትዮጵያ ከሱዳን በቻን ማጣሪያ ሀዋሳ ላይ 1-1 የተለያዩበትን ጨዋታ በረዳት ዳኝነት መርቷል፡፡
ሱዳን ከኢትዮጵያ ኦባያድ ላይ ቅዳሜ ምሽት 2፡00 ሰዓት ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚመሩት ኬንያዊያን ዳኞች ናቸው፡፡ የመሃል ዳኛ አንድሪዊ ጁማ ኦቴኖ ሲሆን ረዳቶቹ ደግሞ ቶኒ ኪዲያ እና ኦሊቨር ኦዲህአምቦ ሁነዋል፡፡ በአራተኛ ዳኛነት ኢዝራኤል ሌማያን ምፓማ ነው፡፡ በ2015 በአዲስ መልክ ከተሰራ በኃላ የአል ሂላል ኦባያድ ክለብ ንብረት በሆነው የኦባያድ ስታዲየም ሱዳን እና ኢትዮጵያ ሲገናኙ ይህ ለሁለተኛ ግዜ ነው፡፡ ፖርቹጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ የመሩት የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በሱዳን አቻው ለአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ (የኦሎምፒክ ማጣሪያ) ለማለፍ 2-0 ኦባያድ ላይ መሸነፉ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *