ዝውውር፡ ኡመድ ኡኩሪ ለስሞሃ ፈረመ

በ2016/17 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃቱን ያሳየው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ኡመድ ኡኩሪ ቀጣይ ማረፊያውን ስሞሃ አድርጓል፡፡ የአሌክሳንደሪያው ክለብ ሌሎች ተፎካካሪ ክለቦችን በመብለጥ ኡመድን ማስፈርም ችሏል፡፡ ኡመድ በስሞሃ ለመቆየት የሶስት አመት ውል ፈርሟል፡፡

ከኤንፒ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት ካፈረሰ በኃላ የካይሮውን ኤል-ኤንታግ ኤል-ሃርቢን በአመቱ መጀመሪያ የተቀላቀለው ኡመድ ምርጥ የውድድር አመት አሳልፏል፡፡ 11 የሊግ ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ የቻለው አጥቂው ምንም እንኳን ኤል-ሃርቢ በሚዋዥቅ አቋም የውድድር ዘመኑን ቢጨርስም በግሉ ነጥሮ በመውጣት በጥሩ መልኩ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል፡፡ ይህንን ተከትሎ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ማረፊያው ወደ ተሻለ ክለብ እንደሚሆን ሲጠበቅ ነበር፡፡

የኡመድ ስም ከታላቁ ዛማሌክ አንስቶ በአውሮፓ ክለቦች ዘንድ ለዝውውር ቢነሳም ስሞሃ ተፎካካሪዎቹን አሸንፎ ተጫዋቾቹን የግሉ አድርጓል፡፡ ስሞሃ እና ኡመድ በዝውውር ጉዳዮች የተስማሙት አስቀድሞ ሲሆን ክለቡ ሌሎች የውጪ ሃገር ተጫዋቾቹን እስኪያሰናብት ድረስ ዝውውሩ ተጓትቶ ቆይቷል፡፡ ኡመድ በአሁኑ ወቅት ወደ ግብፅ አምርቶ ከክለቡ ጋር የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ጀምሯል፡፡

ፎቶ፡ አዛሪያ ተስፋፅዮን

ስሞሃ ስፖርቲግ ክለብ በ1949 እ.ኤ.አ የተመሰረተ ሲሆን በግብፁ ሚልዬኒየር እና የፓርላማ አባል በሆኑት መሃመድ ፋራግ አምር ፕሬዝዳንትነት ይመራል፡፡ የግብፅ የክለቦችን ውድድር ሙሉ በሙሉ ባላንጣዎቹ አል አሃሊ እና ዛማሌክ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ስሞሃ እምብዛም የዋንጫ ድሎች ባይኖሩትም በ2013/14 ዛማሌክን በመብለጥ ሊጉን በሁለተኛነት አጠናቋል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ57 ነጥብ አምስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በቅርብ ግዜያት ውስጥ ክለቡ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሏል፡፡ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በ2017 የተሳተፈው ክለቡ በምድብ ሶስት ከዜስኮ ዩናይትድ፣ አል ሂላል ኦባያድ እና ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ ጋር ተመድቦ ከምድብ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ክለቡ ከውድድር ዘመኑ ማለቅ በኃላ ከአሰልጣኝ ሞሜን ሱሌማን ጋር ተለያይቶ ቼካዊውን ፍራንቼስክ ስትራካ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡ የቀድሞ ቪክቶሪያ ፕሌዘን፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ስሎቫን ብራቲስላቫ እና የቼክ ሪፐብሊክ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስትራካ ያለፈውን የውድድር ዘመን በኤስማኤሊ አሳልፈዋል፡፡

ስሞሃ ለኡመድ አራተኛ የግብፅ ክለቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለኢትሃድ አሌክሳንደሪያ፣ ኤንፒ እና ኤል-ኤንታግ ኤል-ሃርቢ መጫወቱ ይታወሳል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *