ቴዎድሮስ ደስታ የኢትዮጵያ U-20 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተመረጡ

በ2018 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የማጣርያ ጨዋታውን ከኬንያ ጋር የምታደርገው ኢትዮጵያ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ቴዎድሮስ ደስታን ዋና አሰልጣኝ አድርጋ ሾማለች፡፡

በመስከረም ወር መጀመርያ ቀናት ለሚደረገው የመጀመርያ ጨዋታ እስካሁን የአሰልጣኝ ምርጫም ሆነ ዝግጅት ሳያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ አሰልጣኝ ለመምረጥ መስፈርቶችን በማውጣት በቅጥር ማስታወቂያ አማካኝነት በርካታ አሰልጣኞችን ሲያወዳድር የቆየ ሲሆን በመጨረሻም የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታን መርጧል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ጋር በነገው እለት ውል እንደሚፈራረሙ ሲጠበቅ በቀጣይ ቀናት የአሰልጣኙ ረዳቶች ታውቀው ወደ ተጫዋቾች ምርጫ እና ዝግጅት የሚገባ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ላይ የካበተ ልምድ ካላቸው አሰልጣኞች የሚመደቡ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በተለይ ዘንድሮ የገነቡት ቡድን ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ነበር፡፡

በ2016 በፓፓዋ ኒው ጊኒ በተስተናገደው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ እስከ መጨረሻው የማጣርያ ጨዋታ ድረስ ተጉዞ የነበረውና በአሰልጣኝ አስራት አባተ የተመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና በድምር ውጤት ተሸንፎ ሳያልፍ መቅረቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *