የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለፈረንሳይ 2018 የአለም ዋንጫ ማጣርያ ኬንያን መስከረም 7 ይገጥማል፡፡ ለማጣርያው ዝግጅት የበድኑ አሰልጣኝ ሆነው የተመረጡት ቴዎድሮስ ደስታ ስለ ምርጫው ፣ ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ምርጫውን ጠብቀኸው ነበር ?
ምርጫውን መጀመርያውኑ 100% ጠብቄው ነበር፡፡ እርግጠኛም ነበርኩ ፤ ቀኖች ሲቃረቡ ግን የማሰልጠን ፍላጎት የማጣት ነገር መጣ እንጂ በርግጠኝነት እንደምመረጥ አስብ ነበር፡፡ ምክንያቱም የማሰለጥነው ቡድኔ ላይ ካስመዘገብኩት ውጤት በሴቶች እግር ኳስ ላይ ረጅም አመት ከመስራቴ ጋር ተያይዞ እመረጣለው ብዬ ጠብቄ ነበር።
ረጅም ጊዜ በሴቶች እግር ኳስ ከመስራትህ ጋር ተያይዞ አሁን ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነህ መሾምህ ዘግይቷል የሚሉ አሉ ያንተ ምላሽ ምንድ ነው?
አዎ እውነት ነው ዘግይቷል፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ፈጣሪ ይመስገን እዚህ በመድረሴ ደስ ብሎኛል። ዘገየ የምልህ ሴቶች እግር ኳስ ላይ ምን ሰራህ ብትል በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀድሞ በሚዘጋጀው የሴቶች ውድድር ላይ የመጀመርያው ኮከብ አሰልጣኝ ሆኜ የተመረጥኩት እኔ ነኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮዽያ ሻንፒዮናም ላይ በተመሳሳይ ለመጀመርያ ጊዜ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኜ የተመረጥኩት እኔ ነኝ፡፡ ከዛ ቀጥሎ ነው ሌሎች ይህን የኮከብነት እድል ያገኙት፡፡ በኢትዮዽያ ሻንፒዮናም አዲስ አበባ የሴቶች ቡድንን ለመጀመርያ ጊዜ አሸናፊ አድርጌዋለው። ከዚህ ባሻገር በኢትዮዽያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ም/አሰልጣኝ ሆኜ ሰርቻለው፡፡ በአጠቃላይ በሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ አለኝ ።
ክለብ ከማሰልጠን ይልቅ ብሔራዊ ቡድን ማሰልጠን ኃላፊነቱ ከባድ ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣትና ጫናውን ለመቋቋም ምን ያህል ራስህን አዘጋጅተሀል?
በእርግጠኝነት ጫናው አይከብደኝም፡፡ አንዳንድ ከሚዲያ የሚመጡ ጫናዎችን መቋቋም ከቻልክ ስራው በጣም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም የምታውቀው ስራ ነው፡፡ እኔ ከአመድ ላይ ተነስቼ ነው እዚህ የደረስኩት ፤ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖልኝ አይደለም፡፡ በሴቶች እግር ኳስ በመስራቴ በልምዱም ቢሆን በአሰልጣኝነት ላይሰንስም ቢሆን እስከ A ላይሰንስ አለኝ፡፡ ስለዚህ ለሀገሬ የተሻለ ነገር እሰራለው ብዬ አስባለው፡፡ ጫናው ከውጪ ቢመጣም ሁሉ ለተሻለ ነገር ስለሆነ እረዳዋለው፡፡ እኔም ጫናውን ተቋቁሜ ለሀገሬ አንድ ነገር ለመስራት ዝግጁ ነኝ ።
ወደ 20 አመት በታች ቡድኑ እንምጣና ስራህን በይፋ ጀምረሀል፡፡ ለ31 ተጨዋቾችም ጥሪ አድርገሀል፡፡ የተጨዋቾች አመላመል እንዴት ነው ? የዕድሜ ጉዳይስ እንዴት ታይቷል ?
አብዛኛዎቹ አዳዲስ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ በዕድሜ ጉዳይ ለተባለው አምና 20 አመት በታች ኖረው እነሱን ብንመርጥ እድሜያቸው ያለፈ ነው የሚሆነው። እኛ የመረጥነው ከ17 አመት በታች የቡድን የነበሩትንና አዳዲስ ተጨዋቾችን ነው የመረጥነው፡፡ ይህ ማለት እድሜ ላይ ጥሩ ነገር ተሰርቷል። ሆኖም በጣም የምፈልጋቸው ሎዛ አበራ ፣ መዲና አወል ፣ ሰናይት ቦጋለ ፣ ታሪኳ በርገና ሌሎች በርካታ ተጨዋቾች በእድሜ ምክንያት እየፈለኳቸው ወድቀውብኛል። ስለዚህ በዕድሜ ላይ ተገቢ ያልሆ ተጨዋች አልመረጥንም። አመላመሉም በአመት ውስጥ ባሳዩት ብቃታቸው ነው፡፡ እንዲያውም ስማቸውን የማላውቃቸውን በማልያ ቁጥራቸው ጭምር ስመዘግብ ነበር፡፡ የክለቦች አሰልጣኞች ነበር ስማቸውን እየነገሩኝ ስመዘግብ የነበረው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የክለብ አሰልጣኞችን ማመስገን እፈልጋለው።
ዝግጅት ነገ ትጀምራላችሁ፡፡ በዝግጅት ወቅት ምን ለመስራት ታስቧል?
ዝግጅቴን የድርጊት መርሐ ግብር በማውጣት ጀምሬያለው፡፡ ተጨዋቾች ውድድር ተዘግቶ እረፍት ላይ ነው ያሉት፡፡ ውድድር ውስጥ ካልሆኑ ደግሞ ተጨዋቾች በስልጠና ውስጥ ሊሆኑ ላይሆኑም ይችላሉ። በአጠቃላይ ሆኑም አልሆኑም የዝግጅት እና የማቀናጀት ስራ ይጠበቅብናል ፣ የቡድን መንፈስ ስራ ይጠበቃል ፣ ተጨዋቾችን እንደ ቤተሰብ አንድ የማድረግ ስራ ይጠበቃል፡፡
ከጊዜው እጥረት አንፃር እንዲሁም ተጋጣሚያችን ኬንያ አስቀድማ ዝግጅቷን መጀመሯ ጋር ተያይዞ ስራው ፈታኝ ይሆንብኛል ብለህ ታስባለህ?
አዎ፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ሁኔታ ስታስብ ያደረገችውን የአቋም መፈተሻ ስትመለከት በቀጣይም ያሰበችው የወዳጅነት ጨዋታ ስታስብ ተጋጣሚያችን ኬንያ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላትን ቁርጠኝነት ታስባለህ፡፡ ይሄም ቢሆን እኔን አያሳስበኝም፡፡ በዚህ ሀያ ቀናት ውስጥ ቡድኑን ለማቀናጀት በሀገር ወስጥ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር የሚደረግ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ታስቧል፡፡ ይሄ ቡድኑን ለማቀናጀት ይረዳል፡፡ከዝግጅት ጊዜው አጭር ከመሆኑ አንፃር የመጀመርያው ጨዋታ ሊሆን ይችላል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን ቀናት ስለሚኖር ማስተካከል እንችላለን።
ቀድሞ ከሀያ አመት በታች የሴቶች ብሔራው ቡድን እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ድረስ መጓዝ ችሎ ነበር። አንተስ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ምን ታቅዳለህ?
አምና የነበረው ከሀያ አመት በታች ቡድኑ ጥሩ ነበር ፤ መሄድ የሚገባውን ደረጃም ሄዷል፡፡ በሎዛ ስድስት ጎል ታግዞ ቢሆንም ጥሩ ነው። አሁንም እኛ በአዳዲስ ልጆች ከ17 አመት በታች ከነበሩት ተጨዋቾች ጋር በመሆን የተሻለ ነገር ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ያደረገው ምርጫ ትክክለኛ ነው ብዬ አስባለው፡፡ ለሴቶች እግር ኳስ የሰራሁትን ስራ ከግምት በማስገባት ዛሬም ታዳጊዎች ላይ እንድሰራ እድሉን ስለ አመቻቸልኝ ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለው፡፡