የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2009 ዓም ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በኢትየጵያ ሆቴል አከናውኗል። ሐምሌ 12 ቀን ይህ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ በዛሬው እለት ሲደረግ የተለያዩ አጀንዳዎች ተነስተው ለውይይት ቀርበው ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ማሞ ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ገብረማርያም እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኃይሉ ሞላ አለመገኘታቸውን ተከትሎ አቶ በለጠ ዘውዴ መድረኩን ሲመሩት ጠቅላላ ጉባኤው የተጀመረው ምዕላተ-ጉባኤው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኃላ ነበር።
ጉባኤው በክብር እንግድነት በተገኙት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቶ ንጋቱ የመክፈቻ ንግግር ሲከፈት የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንም ተተኪ የእግር ኳስ አመራሮችን ማፍራት እንዳለባቸው እና የመወዳደሪያ ስፍራ ቦታዎችን የማስተካከልና የመስራት ጉዳይ ላይ አትኩሮት ሰጥተው እንዲወያዩ ነበር በንግግራቸው አትኩሮት ሰጥተው የተናገሩት።
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ማሞ ነሀሴ 1 ቀን 2009ዓም ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በላኩት ደብዳቤ በግል ጉዳይ ከፕሬዝዳንትነት እና ከስራ አስፈፃሚው አባልነት ለመነሳት ባቀረቡት ጉዳይ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔውን ማፅደቁን አስታውቋል።
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ሰላሙ በቀለን ከፌደሬሽኑ መታገድን አስመልክቶ በእለቱ ውይይቶች ሲደረግ ፌደሬሽኑ አቶ ሰላሙ በቀለን ያገደበትን ምክንያት ለጠቅላላ ጉባኤው ታዳሚያን አስረድቷል። ለ5ኛ ጊዜ በተደረገው የትምህርት ቤቶች የኮሚኒቲ ውድድር ላይ ካለ አግባብ ከመተዳደሪያ ደምብ ውጪ የዳኞች ምደባ በማድረጋቸው እና እራሳቸውም በአስተባባሪነት ካለ ስራ አስፈፃሚው ውክልና በመገኘታቸው ማገዱን ሲገልፅ ጉባኤውም አቶ ሰላሙ በቀለን ከስራ አስፈፃሚ ቦታቸው አንስቷቸዋል።
ተቀደሚ ምከትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ኃይሉ የቢሮ ስራዎችን በማስተጓጎል እና በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባለመገኘታቸው በሚል ለጠቅላላ ጉባኤው ሃሳብ ቀርቦ እነዚህንም ሁለት ግለሰቦች ጠቅላላ ጉባኤው ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አንስቷቸዋል።
የ2008 ዓም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም የ2009 በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት ሲደረግ በተመሳሳይ የ2009 ዓም በጀት አመት የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ በጉባኤው ፀድቋል።በመጨረሻም ፌደሬሽኑ በቀጣይ አመት የስራ እቅድ ዙሪያ ሃሳቦችን ሲነሱ ፌደሬሽኑም የነበረበትን አንዳንድ ክፍተቶች ማሻሻል እንዳለበት በመተማመን ነበር ጉባኤው የተፈፀመው።