የአስኮ ፕሮጀክት ቅኝት – ክፍል አንድ  

ከተመሰረተበት 1993 ዓ/ም ጀምሮ ያለፉትን 16 አመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጨዋቾችን ከአንደኛ ሊግ አንስቶ እስከ ፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መጫወት የቻሉ ተጨዋቾችን እያፈራ የሚገኘው የአስኮ ፕሮጀክት እየሰራ የሚገኘውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ እና ለወደ ፊት ስለሚያስባቸው እቅዶችን ጨምሮ ሶከር ኢትዮዽያ ፕሮጀክቱ ወደሚከናወንበት አካባቢ በማቅናት ስለ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሰፋ ያለ ጥንቅር በሁለት ክፍል አሰናድታ ያቀረበችውን ዝግጅት በክፍል አንድን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡

ምስረታ

ፕሮጀክቱ ስራ የጀመረው በ1993 አሰልጣኝ አብይ አሸናፊ በተባለ ግለሰብ ተነሳሽነት ሲሆን ያለፉትን 16 አመታት ፕሮጀክቱ በርካታ ታዳጊዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል ።

የተመሰረተበት አላማ እና ምክንያት

የፕሮጀክቱ መሰረታዊ አላማ ታዳጊዎችን በየእድሜ እርከናቸው ለአምስት አመት የሚቆይ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በመስጠት ለክለቦች መመገብ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መመስረት እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ አሰልጣኞች በተጨዋችነት ዘመናቸው ያላሳኩትን ስኬት ታዳጊዎችን በማሰልጠን ስኬታማ አድርጎ ለማብቃት ባላቸው ፍላጎት መነሻነት ነው።

የፕሮጀክቱ አደረጃጀት

ፕሮጀክቱ ሲጀመር በአንድ አሰልጣኝ እና በሃያ ታዳጊ ተጨዋቾች ብቻ ቢሆንም በአሁን ወቅት አደረጃጀቱ ሰፍቶ 18 የስራ አስፈፃሚ አባለት እና 6 አሰልጣኞች ሲኖሩት በሁለቱም ጾታ እድሜያቸው ከ 8 – 17 አመት የሆኑ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ታዳጊዎች ናቸው። ከዚህ ውጭ ሁለት መቶ ሃያ የሚሆኑ ደጋፊዎች በአባልነት ተመዝግበው ይገኛሉ።

የፕሮጀክቱ የስልጠና መንገድ

ፕሮጀክቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን በየጊዜው የተሻሻለ የሚገኙ ዘመናዊ የስልጠና መንገድ የሚከተል ሲሆን ታዳጊዎቹን ብቁ ያደርጋሉ ተብለው የሚታሰቡ በታክቲክ ፣ በቴክኒክ ፣ በስነ-ልቡና እና በአካል ብቃት ረገድ አስፈላጊውን ስልጠና ይሰጣል። በተለይ በክረምት ወራት ታዳጊዎቹ ሙሉ ጊዜ ያላቸው በመሆኑ ከሜዳ ላይ ልምምድ ባሻገር በንድፈ ሀሳብ ተጨማሪ የዘመናዊ እግር ኳስ ስልጠናዎች ይሰጣል።

ወደ ፕሮጀክቱ ታዳጊዎች የሚገቡበት የምልመላ መንገድ

ፕሮጀክቱ የራሱ የሆነ የአመላመል መርህ አለው፡፡በዋናነት እቅድ ፣ ምልመላ ፣ ስልጠና ፣ ውድድር እና ክትትል ሲኖሩት ለምልመላ እንዲረዳው እቅዶችን ካወጣ በኋላ ከተለያዩ አካቢዎች በየእድሜ እርከን መሰረት የሚመጡ ታዳጊዎችን ለምልመላ ያሳትፋል ፤ ያላቸውን ተስጦ በተለያየ መንገድ ከመዘነ በኋላም ወደ ስልጠና እንዲገቡ በማድረግ በሚያገኙት መሰረታዊ ስልጠና በመታገዝ ወደ ክለቦች እንዲያመሩ ያደርጋል።

ፕሮጀክቱ በቆይታው ያሳካው ስኬት

ፕሮጀክቱ በ16 አመት ቆይታ ውስጥ ከ80 በላይ ታዳጊዎችን በፕሮጀክቱ አቅፎ በማሰልጠን ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዲገቡ ማድረግ የቻለ ሲሆን በፕሪምየር ሊግ ፣ በከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ እና ከ17 እና ከ20 አመት በታች ቡድን ላላቸው ለአዲስ አበባ ቡድኖች እየተጫወቱ ይገኛሉ ። ከዚህ ባሻገር ከክለብ አልፈው እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ የተጫወቱ እንደነ ዮናታን ብርሃነ ፣ ዘካርያስ ቱጂ ፣ ከ23 አመት በታች ቡድን ውስጥ የነበረው ሚካኤል በየነ እንዲሁም ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ባህሩ ነጋሽ ያስመረጠ ሲሆን ወደፊትም በርካታ ተጨዋቾችን በስኬት ለክለቦች መመገብ እቅዱ ነው።

የፕሮጀክቱ የገቢ ምንጭ

በመጀመርያ ጅምሩ ላይ ኮንፓሽን በሚባል ድርጅት ለተወሰኑ አመታት እየተደገፈ ይንቀሳቀስ የነበረው ፕሮጀክቱ የኋላ የኋላ ከተለያዩ ግለሰቦች እና ባለ ሀብቶች እንዲሁም መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ተቋማት በሚገኝ ጥቃቅን ድጎማዎች እየሰራ ቢገኝም ፕሮጀክቱ ይህ ነው የሚባል ቋሚ ገቢ የለውም ።

የፕሮጀክቱ ቀጣይ ፈተናዎች

ብዙ መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ቢታመንም በተለይ የበጀት እጥረት ፣ የትጥቅ አቅርቦት ፣ የልምምድ ቦታ ፕሮጀክቱ ወደ ፊት እንደ ፕሮጀክት እንዳይቀጥል ከፍተኛ ፈተናዎች እንደሆነ መረዳት ችለናል።

በክፍል አንድ ይሄን ያህል ስለ ፕሮጀክቱ ምስረታ እና አጠቃላይ አደረጃጀት ምን እንደሚመስል ካስቃኘናቹ በቀጣይ ክፍል ሁለት በሚኖረን ቅኝት የፕሮጀክቱ መስራች እና አሰልጣኝ አብይ እና ከአሰልጣኝ ደስታ ጋር ስለ ፕሮጀክቱ የወደፊት ዕቅድ የሰጡንን ሀሳብ ጨምሮ በስልጠናው ላይ በተገኘንበት ወቅት አስገራሚ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከተመለከትናቸው ተስፈኛ የፕሮጀክቱ ታዳጊ ሰልጣኞች ጋር ያደረግነውን ቆይታ የምናቀርብ ሲሆን በመጨረሻም ሶከር ኢትዮዽያ በቦታው በመገኘት ስለ ፕሮጀክቱ የወደ ፊት ጉዞ ፈተናዎችና ጠቀሚ ሀሳቦችን ከታዘበችው ነገሮች ጋር ይዘን የምንቀርበውን ፅሁፍ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *