የ2009 ኮፓኮካ ኮላ ሀገር አቀፍ ውድድር ተጀምሯል

የ2009 ኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 አመት በታች ውድድር ቅዳሜ በአዲሱ የጅግጅጋ ስታድየም በይፋ ተጀምሯል፡፡ 4 ጨዋታዎችም በእለቱ ተካሂደዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ በሻን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የእለቱ የክብር እንግዶች በተገኙበት በተካሄደው የመክፈቻ ስነስርአት በማርሽ ባንድ የታጀበ የሪባን መቁረጥ ፣ የመክፈቻ ንግግሮች ፣ የተወዳዳሪ ክልሎች በሰልፍ ራስን ማስተዋወቅ እና ሌሎች ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡

05:45 ላይ በመክፈቻው በተደረገው ጨዋታ በወንዶች ኢትዮ ሶማሌ ኦሮሚያን ከፍፁም የእንቅስቃሴ የበላይነት ጋር 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረጉት ኢትዮ ሶማሌዎች አብዱላሂ ሀቢብ ፣ ያሲን ከድር (2) እና አክሊሉ ተሰማ ጎሎች በ4-0 መሪነት ወደ እረፍት ሲያመሩ በሁለኛው አጋማሽ አብዱላሂ ሀቢብ እና ተቀይሮ የገባው አብዱልሀኪም ሀሰን ተጨማሪ ሲያክሉ አሚር አብዶ ለኦሮሚያ አስቆጥረዋል፡፡

በጨዋታው ሁለት ጎል ያስቆጠሩት አብዱላሂ ሀቢብ እና ያሲን ከድር ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡

ቀጥሎ 10:00 ላይ በተካሄደው የወንዶች ጨዋታ የአምናው አሸናፊ ደቡብ ከ ጋምቤላ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ደቡቦች ጨዋታው እንደተጀመረ ብዙም ሳይገፋ አቢ ብርሀኑን በቀይ ካርድ በማጣታቸው አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎድሎ ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደዋል፡፡
ጌን ኡቻላ ጋምቤላን ቀዳሚ ያደረገች ጎል በ18ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር ናትናኤልዮሃንስ– ደቡብን አቻ አድርጎ ወደ እረፍት ሊያመሩ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩ ጋች ዱፕ ጋምቤላን ወደ መሪነት መሎሶ ወደ እረፍት አምርተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ደቡቦች ጥጋቡ ተከተል ባስቆጠረው ጎል ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡

በጨዋታው ከጋምቤላ አቤኚ አባላ እና ጋች ዱፕ ከደቡብ ደግሞ ታረቀኝ አሰፋ መልካም እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

በእለቱ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሜዳ ላይ የሴቶች ጨዋታ የተደረጉ ሲሆን አስተናጋጁ ኢትዮ ሶማሌ በአማራ 5-0 ተሸንፏል፡፡ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ደግሞ የአምናው አሸናፊ ደቡብ ድሬዳዋን 4-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡

የእሁድ መርሀ ግብሮች

ወንዶች (ጅግጅጋ ስታድየም)
03:00 አፋር ከ አዲስ አበባ
05:00 ሐረሪ ከ አማራ
10:00 ትግራይ ከ ቤኒሻንጉል

ሴቶች (መምህራን ኮሌጅ)
1:00 አፋር ከ ሐረሪ
3:00 ኦሮሚያ ከ ጋምቤላ
10:00 ትግራይ ከ ቤኒሻንጉል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *