ጋቶች ፓኖም ተጠባባቂ በነበረበት ጨዋታ አንዚ ማካቻካላ አሸንፏል

በሩሲያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ውጤት ርቆት የቆየው አንዚ ማካቻካላ በሜዳው ድል ቀንቶታል፡፡ አንዚ በሊጉ መጥፎ አጀማመር ማሳየቱን ተከትሎ ወረጅ ቀጠና ውስጥ ተገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያዊው አማካይ ጋቶች ፓኖም በአንዚ ከ21 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ተካቶ ጨዋታዎች እደረገ ሲገኝ ከኤፍሲ ኡፋ ጋር ለነበረው የሊግ ጨዋታ ለሁለተኛ ግዜ በዋናው ቡድን ጋር ተካቶ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተገኝቷል፡፡

አንዚ ከኤፍሲ ኡፋ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአርጀንቲናዊው ሁዋን ሌስካኖ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በውድድር አመቱም ሁለተኛ የሊግ ድል ነው፡፡ ጋቶች በጨዋታው ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ቢገኝም በጨዋታው ላይ ግን ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ በሰኔ ወር ባልተጠበቀ መልኩ ወደ አንዚ ዝውውሩን ያደረገው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ኮከብ በአንዚ ቆይታው በዋናው ሊግ ላይ ጨዋታ ማድረግ ባይችልም በአንዚ ወጣት ቡድን ውስጥ የተሰላፊነት እድል እያገኘ ነው፡፡


ጋቶች አንዚ በሮስቶቭ 1-0 በተሸነፈበት የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ ለመጀመሪያ ግዜ ለክለቡ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበር፡፡ አንዚ በሜዳው ከሁለት ሳምንት በፊት በዳይናሞ ሞስኮ 3-1 ከተረታ በኃላ አሰልጣኙን አሌክሳንደር ግሪጎሪያንን አንስቶ በቫዲም ስክሪፕቼንኮ ተክቷል፡፡ ስክሪፕቼንኮ ከሳምንት በፊት በሩቢን ካዛን የ6-0 ሽንፈት የአንዚ ቆይታቸውን ሲጀምሩ በሁለተኛ ጨዋታቸውን ክለቡ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ አንዚ ለ8 ጨዋታዎች 6 ነጥቦችን ሰብስብ 16 ክለቦች የሚወዳደሩበት የሩሲያ ሊግ 15ኛ ነው፡፡ ሊጉን በቀድሞ የሳምፕዶሪያ እና ላዚዮ ኮከብ ሮቤርቶ ማንቺኒ የሚመራው ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግ በ20 ነጥብ ሲመራ ሎኮሞቲቭ ሞስኮ፣ ኤፍኬ ሮስቶቭ እና ወደ ዮሮፓ ሊግ ምድብ በሬድ ስታር ቤልግሬድ ተሸንፎ የተሰናበተው ኤፍኬ ክራስኖዳር በእኩል 15 ነጥብ ከ2-4 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው የአምናው ቻምፒዮን ስፖርታክ ሞስኮ በ9 ነጥብ 9ኛ ላይ ይገኛል፡፡

በ9ኛ ሳምንት ጨዋታ አንዚ ማካቻካላ ከሜዳው ውጪ ወደ ቬሊኬይ ኖቭጎሮድ አቅንቶ ኤፍሲ ቶስኖን ከቤሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ በኃላ ያደርጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *