የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈረንሳይ ለምታስተናግደው የ2018 የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ከኬንያ አቻው ላለበት የመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም ዝግጅቱን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ዋና አሰልጣኝነት እየተመራ 30 ተጫዋቾችን በመያዝ ነሐሴ 18 በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ጥሪ ቀርቦላት ካልመጣችው የኤሌክትሪኳ ተከላካይ ሳምራዊት ኃይሉ ውጪ ለሁለት ቀናት በጂም እና የሜዳ ተግባራት ላይ ያተኮረ ስራን ሲሰሩ ቆይተው ቅዳሜ ጠዋት ወደ ሀዋሳ በማቅናት ሴንትራል ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ ልምምዳቸውን በመጡበት ቅዳሜ ከሰአት በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም እና በጂም ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ትላንት እና ዛሬ ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋት 3:00 – 05:00 የኢንዱራንስ እና ታክቲክ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ ከሰአት 10:00 ላይ በሁለተኛው የልምምድ ጊዜያቸው ኳስን መሰረት ያደረገ አጨዋወት እና በሁለት ተከፍለው ልምምድ ሰርተዋል፡፡
አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ምንም አይነት ችግር እንዳላገጠማቸው እና መልካም የሚባል ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀው 31 ተጫዋቾች ጠርተው ከሳምራዊት ኃይሉ ውጭ ሁሉም ሲሰሩ ቆይተው ትላንት ስድስት ተጫዋቾች መቀነሳቸውን ለሶከር ኣትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ አሁን 24 ተጫዋቾች ልምዳቸውን እየሰሩ ሲሆን የተቀነሱት ከአርባምምጭ የተመረጡት መስከረም ኢሳያስ ፣ ትዝታ ፈጠነ እና ሳራ ኬዲ ከአካዳሚ ዘነበች ዘመዱ ፣ ከኤሌክትሪክ ሰናይት አስራት እና ከሀዋሳ ከተማ ነፃነት መና መሆናቸው ታውቋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከካሜሩን አልያም ከታንዛኒያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ኬንያ የመጀመርያ ጨዋታ መስከረም 7 በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ መስከረም 22 በኬኒያ ይደረጋል፡፡