ሩሲያ በ2018 ለምታስተናግደው የፊፋ የአለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን የሚደረጉ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል፡፡ በምድብ አንድ ኮናክሬ ላይ ጊኒ ሊቢያን ስታስተናግድ ካምፓላ ላይ ምድብ አምስት አናት ላይ የተቀመጡት ግብፅ እና ዩጋንዳ ይገናኛሉ፡፡
የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቻቸውን በሽንፈት የጀመሩት ጊኒ እና ሊቢያ ወደ አለም ዋንጫው ለማለፍ ያላቸውን ተስፋ እንዳይሟጠጥ ወሳኝ የሆነ ጨዋታ ኮናክሬ ላይ ያደርጋሉ፡፡ ሁለቱም ሃገራት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቱኒዚያ የተረቱት ሃገራቱ በቀናት ልዩነት የሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ ቢያንስ የማለፍ ተስፋ ላይ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ምድቡን ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቱኒዚያ በእኩል 6 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመሩታል፡፡ ሊቢያ አልጄሪያ በቻን ማጣሪያ ያሸነፈውን ቡድን በአብዛኛው ስታካትት ጊኒ በቡኩሏ በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ወሳኝ ተጫዋቾቿ ለጨዋታው ዝግጁ ሁነዋል፡፡
ከሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች “ሚቾ” ሚሉቲን ጋር በሐምሌ ወር የተለያየችው ዩጋንዳ በግዜያዊ አሰልጣኙ ሞሰስ ባሴና እየተመራች ግብፅን ካምፓላ ላይ ታስተናግዳለች፡፡ ለጨዋታው ባሴና የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአሁኑ የዛምቢያው ቢዩልድኮን የተከላካይ ክፍል ተጫዋች አይዛክ ኢዜንዴ እና በሮማንያ የሚጫወተው ዊሊያም ሉዋጋ ኪዚቶን ጠርተዋል፡፡ ኪዚቶ ከአፍሪካ ዋንጫ በኃላ ከሚቾ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እሯሱን ከብሄራዊ ቡድን አግልሎ ነበር፡፡ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ለኬፕ ቨርድ ጋር ፕራያ ላይ የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጉዳት ካመለጠው በኃላ አሁን ላይ ወደ ክሬንሶቹ የቡድን ስብስብ ተመልሷል፡፡ የግብፅ አልሰጣኝ ሄክቶር ኩፐር አስጊ የሚባል ጉዳት በቡድናቸው የሌለ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መልካም አጀማመር ያሳዩትን መሃመድ ሳላህ እና አህመድ ሄጋዚን አካተዋል፡፡ ግብፅ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በቱኒዚያ በሰኔ ወር የተሸነፈች ሲሆን ከ1990 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ አለም ዋንጫ ለማለፍ በአራት ቀናት ልዩነት ዩጋንዳን መርታት እድሏን ያሰፋዋል፡፡ ሁለቱ ሃገራት በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ጨዋታ ተገናኝተው ግብፅ አብደላ ኤል-ሰዒድ ብቸኛ ግብ ማሸነፏዋ አይዘነጋም፡፡ ምድብ አምስት ግብፅ በስድስት ነጥብ ስትመራ ዩጋንዳ በአራት ትከተላለች፡፡ ጋና በአንድ እንዲሁም ኮንጎ ብራዛቪል ያለምንም ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች
16፡00 – ዩጋንዳ ከ ግብፅ (ማንዴላ ናሽናል ስታዲየም)
17፡00 – ጊኒ ከ ሊቢያ (ስታደ 28 ሴፕቴምበር)
አርብ ነሃሴ 26
15፡30 – ጋና ከ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ባባ ያራ ስፖርትስ ስታዲየም)
17፡00 – ናይጄሪያ ከ ካሜሮን (አክዋ ኢቦም ስታዲየም)
17፡30 – ኬፕ ቨርድ ከ ደቡብ አፍሪካ (ፕራያ ስታዲየም)
21፡00 – ቱኒዚያ ከ ዲ.ሪ. ኮንጎ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)
21፡00 – ሞሮኮ ከ ማሊ (ኮምፕሌክስ ፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም)
ቅዳሜ ነሃሴ 27
15፡00 – ዛምቢያ ከ አልጄሪያ (ሂሮስ ናሽናል ስታዲየም)
17፡00 – ጋቦን ከ ኮትዲቯር (ስታደ ፍራንስቪል)
20፡00 – ሴኔጋል ከ ቡርኪና ፋሶ (ስታደ ሊዮፖልድ ሴዳር ሰንጋሆር)