=> ድሬደዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በበኩሉ ስለ ይቅርታ መጠየቁ የማውቀው ነገር የለም ይላል፡፡
በ2009 የውድድር ዘመን ለአዳማ ከተማ በመጫወት ያሳለፈውና ከአዳማ ከተማ ጋር ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ድሬዳዋ በነበረው ቆይታ ለድሬዳዋ ከተማ ለመጫወት የስምምነት ፊርማውን ያኖረው ብሩክ ቃልቦሬ ሐምሌ 5 የሀገር ውስጥ ተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከተከፈተ በኋላ ለወልድያ እግርኳስ ክለብ ፊርማውን ማኖሩን ተከትሎ በተጫዋቹና በድሬዳዋ ከተማ መካከል ውዝግብ መፈጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ ድሬዳዋ ከተማ ብሩክ ለክለቡ አልፈረምኩም ከማለቱ ባሻገር ለመገናኛ ብዙሀን የከተማውን እና የክለቡን ገፅታ የሚያጎድፍ ያልተገባ መግለጫ ሰጥቷል በማለት ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ለቅሬታው እና ለተፈጠረው ስህተት ብሩክ ቃልቦሬ ዛሬ በይፋ በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመቅረብ ለድሬደዋ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን የይቅርታ ደብዳቤ አስገብቷል።
” ለሁለት ክለብ መፈረሜ ከግንዛቤ ችግር ፣ ለእድገት ካለኝ ጉጉት እና ከግል ድክመት በመነሳት የፈፀምኩት ስህተት በመሆኑ የድሬዳዋ ከተማ እግርኳስ ክለብ አመራሮች ይቅር ባይ የእግር ኳስ ወዳድና የፍቅር ከተማ በሆነው የድሬደዋ ህዝብ ስም ልባዊ ይቅርታ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ፡፡ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የፈፀምኩት ስህተት ተገቢ እንዳልሆነ እና ያለኝን ጉጉትና ዝግጅት ከግምት በማስገባት ይቅርታ እንዲያደርግልኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለው” ሲል በደብዳቤው ገልጿል፡፡
ብሩክ ቃልቦሬ ያስገባውን የይቅርታ ደብዳቤ በፋክስ ለድሬደዋ እግር ኳስ እንደላከ ቢያሳውቅም ለድሬዳዋ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተላከ ስለተባለው የይቅርታ ደብዳቤ ክለቡ ምንም እንደማያውቅ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል ።
የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሩክ ቃልቦሬ ላስገባው የይቅርታ ደብዳቤ በፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጥና የተፈጠረው ችግር በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያገኝ አሳውቋል ።