በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ዩጋንዳ እና ጊኒ ወሳኝ የሆነ ድልን በሜዳቸው አስመዝግበዋል፡፡ ዩጋንዳ ግብፅ 1-0 ስትረታ ጊኒ ሊቢያን 3-2 አሸንፋለች፡፡
በምድብ አንድ ጊኒ ሊቢያን በመርታት ከመሪዎቹ ጋር ያላትን የነጥብ ልዩነት ለግዜውም ቢሆን ወደ ሶስት አጥብባለች፡፡ ጊኒ የማሸነፉን ቅድመ ግምት እንደማግኘቷ በጨዋታው የሰሜን አፍሪካ ተጋጣሚዋ ላይ የሙከራም ይሁን የጨዋታ ብልጫን በመጀመሪያው አጋማሽ ወስዳለች፡፡ ነገር ግን እንግዶቹ በሁለተኛው 45 በተለይ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ጊኒን አጣብቂኝ ውስጥ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከተው ነበር፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ወደ ሊቨርፑል ከጀርመኑ አርቢ ላይፕዢሽ ለመዘዋወር የተስማማው ናቢ ኬይታ ጊኒን በ7ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሲያደርግ አቡበከር ካማራ በ22ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ 72ኛው ደቂቃ ናቢ ኬይታ የመታውን የፍፁም ቅጣት ምት የሊቢያው ግብ ጠባቂ መሃመድ ናስኑሽ ሲመልስበት በዚህ የተነቃቁት እንግዶቹ በ87 እና 88ኛው ደቂቃዎች ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ባልተጠበቀ መልኩ የኮናክሬ የአቻ ውጤትን ይዘው የሚመሉ አስመስሎታል፡፡ ሙታሲም ሳቡ እና አክራም ዙዌይ በደቂቃ ልዩነት ከመረብ ያገኗኛቸው ኳስ ሊቢያን አቻ አድርጓል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ አልካላይ ባንጉራ ጊኒን የታደገበትን ኳስ አስቆጥሯል፡፡ ምድብ አንድን ዲ.ሪ.ኮንጎ እና ቱኒዚያ በእኩል ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሲመሩ ጊኒ በሶስት ሊቢያ ያለምንም ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
ካምፓላ ላይ ዩጋንዳ ግብፅ 1-0 በመርታት የምድብ አምስት መሪነትን ከባለሪከርድ የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ተቀብላለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ሃገራት የግብ እድሎችን መፍጠር ሲችሉ በተለይ ክሬንሶቹ በኢማኑኤል ኦክዊ እና ዴሪክ ኒሲምባቢ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ ለአብዛኞቹ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ የፈርኦኖቹን ኮከቦች መሃመድ ሳላህ እና መሃመድ ኤልኒኔን እንዳይንቀሳቀሱ የገቱበትን መንገድ ለአሸናፊነት አብቅቷቸዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ከንሲምባቢ በግንባሩ የጨረፈውን ኳስ ተቆጣጥሮ ሁለት የግብፅ ተከላካዮች አታሎ በማለፍ በግራ እግሩ አክርሮ የመታው ኳስ የኤሳም ኤል ሃድሪ መረብ ላይ አርፎ ዩጋንዳ መሪ መሆን ችላለች፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ግብፅ የአቻነት ግብ ፍለጋ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በተለይ ሳላህ ሞክሮ ዴኒስ ኦኒያንጎ ያመከነበትን እድል የሚጠቀስ ነው፡፡ ምድቡን ዩጋንዳ በሰባት ስትመራ ግብፅ በስድስት ትከተላለች፡፡
ውጤቶች
ዩጋንዳ 1-0 ግብፅ
ጊኒ 3-2 ሊቢያ
አርብ ነሃሴ 26
15፡30 – ጋና ከ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ባባ ያራ ስፖርትስ ስታዲየም)
17፡00 – ናይጄሪያ ከ ካሜሮን (አክዋ ኢቦም ስታዲየም)
17፡30 – ኬፕ ቨርድ ከ ደቡብ አፍሪካ (ፕራያ ስታዲየም)
21፡00 – ቱኒዚያ ከ ዲ.ሪ. ኮንጎ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)
21፡00 – ሞሮኮ ከ ማሊ (ኮምፕሌክስ ፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም)
ቅዳሜ ነሃሴ 27
15፡00 – ዛምቢያ ከ አልጄሪያ (ሂሮስ ናሽናል ስታዲየም)
17፡00 – ጋቦን ከ ኮትዲቯር (ስታደ ፍራንስቪል)
20፡00 – ሴኔጋል ከ ቡርኪና ፋሶ (ስታደ ሊዮፖልድ ሴዳር ሰንጋሆር)