የኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 አመት በታች ሀገር አቀፍ ውድድር በጅግጅጋ ከተማ መካሄዱን ቀጥሎ በዛሬው እለት ወደ ፍጻሜ የተሸጋገሩ ቡድኖች ተይተዋል፡፡ ኢትዮ ሶማሌ እና አማራ በወንዶች ፤ ደቡብ እና አማራ በሴቶች ለፍጻሜ የደረሱ ክልሎች ሆነዋል፡፡
ወንዶች
አዲስ በተገነባው የጅግጅጋ ስታድየም 08:00 ላይ የአስተናጋጁ ክልል ቡድን የሆነው ኢትዮ ሶማሌ አፋር ክልልን 1-0 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል፡፡ ኢትዮ ሶማሌ በሜድብ ጨዋታዎቸ ተጋጣሚዎቹ ላይ 18 ጎሎች እንደማስቆጠሩ ከፍተኛ ግምት ቢሰጠውም ከአፋር እጅግ ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡
ከሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በኩል ቀይ ካርድ ያስመዘዘ ከፍተኛ ጉሽሚያ እና እና እልህ የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ በታየበት በዚሀ ጨዋታ ኢትዮ ሶማሌዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም የአፋርን የተከላካይ መስመር መስበር ተስኗቸው ቆይተው በመጨረሻም በ72ኛው ደቂቃ ጀማል ካሊድ ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፈው ለፍጻሜው አልፈዋል፡፡
በዚሁ ስታድየም ቀጥሎ በተደረገው ጨዋታ አማራ ድሬዳዋን 5-2 አሸንፎ የኢትዮ ሶማሌ ተጋጣሚ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር የተስናገደበት ሲሆን የሁለቱም ቡድን ሴት ተጫዋቾች ሞቅ ያለ ድጋፍ በመስጠት ቡዶናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል፡፡
የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥቂት የጎል ሙከራ የተስተናገደበት ተመጣጣኝ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን ግብም ሳይስተናገድበት ወደ እረፍት አምርተዋል፡፡
7 ግቦች በተቆጠሩበትና ለተመልካች አዝናኝ በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ አማራ ክልል የበላይነቱን አሳይቶ 5-2 ማሽነፍ ችሏል፡፡ ለአማራ ጎሎቹን ኤልያስ ጌታቸው ፣ አዳነ ያለው ፣ ከድር አሊ ፣ ወንድወሰን ፈንታ እና ሚካኤል ሁነኛው ሲያስቆጥሩ አሚር ሻሚል እና ግርማ ሞገስ ለድሬዳዋ አስቆጥረዋል፡፡
የፍጻሜው ጨዋታ እሁድ ሲደረግ አስተናጋጁ ኢትዮ ሶማሌ ክልል ከአምናው የፍጻሜ ተፋላሚ አማራ ክልል ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
ሴቶች
በዶ/ር አብድልመጂድ ሁሴን የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ግቢ 8:00 ላይ የተደረገው የአማራ እና ኦሮሚያ ጨዋታ በአማራ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የአማራን የድል ጎሎች ሐረግ ሙሉ በ17ኛው እንዲሁም እስከዳር አወቀ በ32ኛው ደቁቃ አስቆጥረዋል፡፡
ቀጥሎ በዛው ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ደቡብ አዲስ አበባን 3-1 በማሽነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል፡፡ አምሳለ ፍስሀ በ8ኛው ደቂቃ ደቡብን ቀዳሚ ስታደርግ በውድድሩ ምርጥ አቋሟን እያሳየች የምትገኘው ቃልኪዳን ሊቁበሸዋ አዲስ አበባን አቻ አድርጋለች፡፡ በ38ኛው ደቂቃ ደቡብ በድጋሚ በአምሳል ፍስሀ ጎል ወደ መሪነት ሲመለስ በ68ኛው ደቂቃ አምሳል ፍስሀ በውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሐት-ትሪክ በመስራት የደቡብን አሸናፊነት ያረጋገጠች ጎል አስቆጥራለች፡፡
የሴቶች ፍጻሜ ጨዋታ እሁድ ሲደረግ በምድብ ሀ ተደልድለው የነበሩትና በተመሳሳይ 7 ነጥቦች ከምድባቸው ያለፉት አማራ እና ደቡብ ክልሎች ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ፡፡ በምድብ ጨዋታ በተገናኙበት ወቅት 3-3 ሲለያዩ ለየቡድኖቻቸው ሐት-ትሪክ የሰሩት አምሳል ፍስሀ (ደቡብ) ትዕግስት ወርቄ (አማራ)ም በፍጻሜው የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡