በአለም ዋንጫ ማጣርያ ኮትዲቯር የምድብ መሪነቷን ስታጠናክር ዛምቢያ አልጄሪያን ረታለች

የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የአፍሪካ ዞን ሶስተኛ የምድብ ጨዋታዎች ቅዳሜ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ኮትዲቯር የምድብ መሪነቷን ያጠናከረችበትን ድል ጋቦን ላይ ስታስመዘግብ በ10 ተጫዋች ሁለተኛ አጋማሽን የጨረሰችው ዛምቢያ አልጄሪያ ረታለች፡፡ ሴኔጋል በሜዳዋ በቡርኪና ፋሶ ነጥብ ጥላለች፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ የመሃል ዳኞች ባምላክ ተሰማ በዋና ዳኛነት እንዲሁም ሃይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኛነት በመሩት ጨዋታ ሊበርቪል ላይ ኮትዲቯርን ያስተናገደችው ጋቦን 3-0 ተሸንፋለች፡፡ በመጀመሪያው 45 ግብ ባልተስተናገደበት የሃገራቱ ጨዋታ የዝሆኖቹን የድል ግቦች ማክስ አሊያን ግራድል እና ሰይዱ ዶምቢያ (2) ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ ኮትዲቯር በሁለተኛው አጋማሽ ከወሰደችው ብልጫ አንፃር ድሉ የተገባ ነበር፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው በሽንፈት የጀመሩት ለአሰልጣኝ ማርክ ዊልሞት ድሉ በትንሹም ጫና ያቀልላቸዋል፡፡ ምድብ ሶስት ኮትዲቯር በ7 ነጥብ ስትመራ ሞሮኮ በ5 ትከተላለች፡፡
ወደ ዳካር ያቀናችው ቡርኪና ፋሶ ወሳኝ የሆነ ነጥብ ከሴኔጋል ጋር አቻ በመለያየት ይዛ ተመልሳለች፡፡ ያለግብ በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ የሰይዶ ማኔ፣ ሙሳ ሶ እና ኬይታ ባልዴ ዲያዎ የተዋቀረው የቴራንጋ አንበሶቹ የአጥቂ መስመር የቡርኪና ፋሶ የተከላካይ መስመርን መስበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ በጨዋታው ላይ ሙሳ ሶ ከሴኔጋል እንዲሁም በርትራንድ ትራኦሬ እና ፕሪጁስ ናኮልማ ከቡርኪና ፋሶ በኩል ያደረጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂዎቹ ካዲም ንዳዬ እና ወደ ፈረንሳዩ ሊል በክረምቱ የዝውውር መስኮት በተዛወረው ሄርቬ ኮፊ አማካኝነት ግብ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩ የሴኔጋሉ የመሃል ተከላካይ ካሊዱ ኩሊባሊ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ምድብ አራትን ቡርኪና ፋሶ በ5 ነጥብ ስትመራ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ በእኩል 4 ነጥብ እንዲሁም ኬፕ ቨርድ በ3 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
በምድብ ሁለት የ2014 የአለም ዋንጫ ተሳታፊዋ አልጄሪያ ከወዲሁ የማለፍ ተስፋዋ የተማጠጠበትን ሽንፈት ሉሳካ ላይ በዛምቢያ አስተናግዳለች፡፡ 3-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ቺፖሎፖሎዎቹ በብሪያን ምዌላ ሁለት ግቦች 2-0 የመጀመሪያው አጋማሽ መምራት የቻሉ ሲሆን ያሲን ብራሂሚ ልዩነቱን በ53ኛው ደቂቃ ማጥበብ ችሎ ነበር፡፡ ከ2 ደቂቃች በኃላ የዛምቢያው ወጣት አጥቂ ፋሽን ሳካላ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲሰናበት ቀሪዎቹን ደቂቃዎቹ ባለሜዳዎቹ በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል፡፡ የቁጥር ብልጫ የነበራቸው አልጄሪያዎች ግቦችን ለማግኘት ተጭነው ቢጫወቱም ውጤት ለመቀየር ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ተቀይሮ የገባው ኢድሪስ ሳዲ የሞከረው ኳስ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታካ ስትወጣ በመልሶ ማጥቃት የተዳከመውን የአልጄሪያ የተከላካይ ክፍል በግልፅ ያገኙት ዛምቢያዎች በኤኖክ ምዌፑ ግብ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል፡፡ ምዌፑ እና ሳካላ ዛምቢያ በያዝነው ዓመት የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ቻምፒዮን ስትሆን እና በፊፋ የአለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ጥሩ ግስጋሴን ስታደርግ ለቡድኑ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ተጫዋቾ ናቸው፡፡ ምድቡን የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ለማረጋገጥ የተቃረበችው ናይጄሪያ በ9 ነጥብ ስትመራ ዛምቢያ በ4፣ ካሜሮን በ2 እና አልጄሪያ በ1 ይከተላሉ፡፡
የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ሰኞ መደረግ ሲጀምሩ በምድብ አንድ ቱኒዚያ ላይ ሊቢያ ጊኒን ታስተናገዳለች እንዲሁም ካሜሮን ናይጄሪያን ትገጥማለች፡፡ በርከት ያሉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ማክሰኞ ይደረጋሉ፡፡
ውጤቶች
ዩጋንዳ 1-0 ግብፅ
ጊኒ 3-2 ሊቢያ
ጋና 1-1 ኮንጎ ሪፐብሊክ
ናይጄሪያ 4-0 ካሜሮን
ኬፕ ቨርድ 2-1 ደቡብ አፍሪካ
ቱኒዚያ 2-1 ዲ.ሪ. ኮንጎ
ሞሮኮ 6-0 ማሊ
ዛምቢያ 3-1 አልጄሪያ
ጋቦን 0-3 ኮትዲቯር
ሴኔጋል 0-0 ቡርኪና ፋሶ

ቀጣይ ጨዋታዎች

ሰኞ ነሃሴ 29
18፡00 – ካሜሮን ከ ናይጄሪያ (ስታደ ኦምኒስፖርትስ አማዱ አሂጆ)
20፡00 – ሊቢያ ከ ጊኒ (ስታደ ሙስጠፋ ቤን ጃኔት)

ማክሰኞ ነሃሴ 30
15፡30 – ኮንጎ ሪፐብሊክ ከ ጋና (ስታደ ኪንቴሌ 3)
17፡30 – ኮትዲቯር ከ ጋቦን (ስታደ ደ ባኩ)
18፡00 – ቡርኪና ፋሶ ከ ሴኔጋል (ስታደ ኦገስት 4)
18፡30 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ ቱኒዚያ (ኮምፕሌክስ ኦምኒስፖርትስ ስታደ ደ ማርቲርስ)
19፡00 – ማሊ ከ ሞሮኮ (ስታደ 26 ማርስ)
19፡00 – ደቡብ አፍሪካ ከ ኬፕ ቨርድ (ሞሰስ ማቢዳ ስታዲየም)
20፡00 – ግብፅ ከ ዩጋንዳ (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)
21፡30 – አልጄሪያ ከ ዛምቢያ (ስታደ መሃመድ ሃምላዊ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *