የሴቶች ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለኬንያው ጨዋታ ዝግጅቱን ቀጥሏል

የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ፈረሳይ በ2018 ለምታስተናግደው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከኬንያ ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ዝግጅቱን በሀዋሳ ከተማ አጠናክሮ በመቀጠል ላይ ይገኛል።

በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ለ31 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ በአዲስ አበባ በኋላም በሀዋሳ ከተማ ማረፊያውን ሴንትራል ሆቴል በማድረግ ዝግጅቱን ሲያከናውን ቆይቷል። ያለፉት 15 ቀናት በነበረው ቆይታ የዝግጅታቸው የመጀመርያ እቅድ በነበረው ጊዜ ተጨዋቾቹ ከውድድር ርቀው እንደመቆየታቸው የቴክኒክ ፣ የትንፋሽ ፣ የአካል ብቃት በጂም ጨምሮ በቀን ሁለቴ ልምምድ ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ክለቦች የመጡ ተጨዋቾች በመሆናቸው የብሔራዊ ቡድን ስሜት የመፍጠር ስራ እንደተሰራ ተገልጿል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ቡድኑ የተጨዋቾችን ቁጥር ከ31 ወደ 24 በማውረድ እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ብሔራዊ ቡድኑ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሁለተኛ የልምምድ ምዕራፍ የተሻገረ ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ከኳስ ጋር ያተኮሩ ልምምዶችን በተጓዳኝ የቡድኑን ውህደት እና አቅም ለመለካት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን በማድረግ የቡድኑን ጥንካሬ እና ደካማ ጎን ለማወቅ እንደሚሰሩ ታውቋል ።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን በቀጣይ አመት በደደቢት ማልያ የምንመለከታት አጥቂዋ ትደግ ፍስሀ ከጉዳቷ ጋር እየታገለች ስትገኝ ለጨዋታው ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ሰምተናል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ እንደተናገሩት የብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እስካሁን የተሳካ እንደሆነ ገልፀው በሆቴል ፣ በመስተንግዶ ፣ በትጥቅ አቅርቦት ያጋጠመ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በማከልም የልጆቹ ዲሲፕሊን ፣ ሀገራቸውን ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት ፣ ለጨዋታው የሰጡት ግምት ፣ የሚሰጣቸውን ልምምድ በአግባቡ በመስራት እያሳዩ ያሉት ተነሳሽነት አጠቃላይ የአሰልጣኝ ስታፉን በሙሉ ያስገረመ እና ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቋም መፈተሻ ጨዋታ ከታንዛንያ ጋር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ እንዳልመጣ የገለፁት አሰልጣኝ ቴዎድሮስ የዘገየ የአጭር ጊዜ ዝግጅት ማድረጋቸው ብዙም ችግር እንደሌለውና በሚችሉት አቅም ሁሉ ጨዋታውን በድል ለመወጣት እየተዘጋጁ እንደሆነ ገልፀው የተጋጣሚያቸው ኬንያ ዝግጅት እና ሌሎች ነገሮችም ስጋታቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በመረሻም ከፓስፖርት እና ከሌሎች ነገሮች ጋር ተያይዞ ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ም/ኃላፊ መሰከረም ታደሰ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ለመጨረስ እየሰሩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የኢትዮዽያ ከሃያ አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከኬንያ ጋር በሀዋሳ አለም አቀፍ ስቴድየም መስከረም 7 የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን የዕለቱን ጨዋታ የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከሩዋንዳ ፣ ኮሚሽነሩ ከጅቡቲ እንደሚሆኑ ካፍ አሳውቋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *