የዛሬው የቡና ጋዜጣዊ መግለጫ…

ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊው ድራጋን ፖፓዲችን የክለቡ አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን ተከትሎ ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዱ ፣ ፕሬዝዳንቱ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ፣ አሰልጣኝ ፖፓዲች እና የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ደሳለኝ ግርማ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተነሱትን ሃሳቦች በርእስ ከፋፍለን እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

 

 

‹‹ በምስራቅ አፍሪካ የማሰልጠን ልምድ ያለው ፖፓዲችን መርጠናል›› አቶ ገዛኸኝ ወልዱ

 

‹‹ የአሰልጣኝ ቡድኑን እንደ አዲስ በማደራጀት ላይ እንገኛለን፡፡ የውድድር ዘመኑን ገምግመን ክለቡን እንደ አዲስ በአሰልጣኞች ማደራጀት እንዳለብን ተነጋግረን በቅድሚያ የቴክኒክ ዳይሬክተር ቀጥረናል፡፡ ከአለም አቀፍ ኤጀንቶች ጋር በመነጋገርም በርካታ አሰልጣኞችን ተመልክተናል፡፡ በአውሮፓ እና በመካከለኛቀው ምስራቅ ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች ያሉ ሲሆን በአፍሪካ የመስራት ልምድ ያላቸው አሰልጣኞችም አሉ፡፡ እኛም በምስራቅ አፍሪካ የማሰልጠን ልምድ ያለው ፖፓዲችን መርጠናል፡፡ በክለብ አደረጃጀት ከእኛ ብዙም ባልራቁት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ስለሰራ በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደማይገጥመው እንገምታለን፡፡ ››

‹‹ አንዋር ያሲን የፖፓዲች ረዳት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ከአሰልጣኙ ብዙ ልምድ ይቀስማል ብለንም እናስባለን፡፡ በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነትም ውብሸት ደሳለኝ ይቀጥላል፡፡ አሁን የሚቀረን የቡድን መሪ መመደብ ብቻ ነው፡፡ ››

‹‹ ደሳለኝ በህፃናት እና ወጣት ተጫዋቾች ላይ ልምድ ስላለው ቴክኒካል ዳይሬክተር አድርገን ሾመነዋል፡፡ በፊፋ የተቀመጠውን የቴክኒክ ዳይሬክተር የስራ ሃላፊነት ወደ አማርኛ በመተርጎም 21 የስራ ኃላፊነቶችን አስቀምጠንለታል፡፡ ይህንንም ያደረግነው የስራ ኃላፊነቱ ድንበር እንዲኖረውና አንዱ በሌላኛው የስራ ድርሻ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ በሚል ነው፡፡ ››

‹‹ አሰልጣኝ ፖፓዲችን እንደሁኔታው የሚታደስ የ1 አመት ኮንትራት ሰጥተናቸዋል፡፡ ››

‹‹ ኮንትራት ያላቸው 18 ተጫዋቾች ከኛ ጋር ይቀጥላሉ፡፡ አሰልጣኝ አንዋር ተጫዋቾቹን ስለሚያውቃቸው ለአሰልጣኙ አስቸጋሪ አይሆኑም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከ20 አመት በታች እና ከ17 አመት በታች ቡድኖች ያደረጉትን ጨዋታ እንደሚለከቱ አድርገናል፡፡ ››

‹‹ ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አጨዋወት ከውጤት ጋር መጣመር አለበት፡፡ ››

 

DSC01057

 

‹‹ እቅዳችን በሁሉም የእድሜ እርከኖች ያሉ ቡድኖች አጨዋወት ተመሳሳይ እንዲሆን ማድረግ ነው ›› ደሳለኝ ግርማ

 

‹‹ ዋናው ስራዬ አሰልጣኝነት ነው፡፡ ነገር ግን ከ18 አመት በላይ በእግርኳሱ ዙርያ ቆይቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያውያን ስፖርት ማህበር ላይ ከ11 አመት በላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ ለ4 አመታት ደግሞ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ማህበሩን አገልግያለሁ፡፡ ››

‹‹ የክለቡ ፍላጎት በዋናው ቡድን ላይ ውጤት እንዲመጣ ነው፡፡ ክለቡ ውጤት እንዲያመጣ ዘመናዊ አሰራር ያስፈልጋል፡፡ እቅዳችን እና ከአሰልጣኙ ጋር የተነጋገርነውም በሁሉም የእድሜ እርከኖች ያሉ ቡድኖች አጨዋወት ተመሳሳይ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ››

 

DSC01058

‹‹ ፖፓዲች የዘልማድ አሰራሮችን እንዲቀይሩ ነው የቀጠርናቸው ›› መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ

‹‹ ሀገር ውስጥ ያሉ አሰልጣኞችን አወዳድረናል፡፡ ሁለት እና ሶስት የሚሆኑትን ደግሞ በአካል አነጋግረናል፡፡ ያቀረብናቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉ ልናገኝ ግን አልቻልንም፡፡ ››

‹‹ አመቱ ሲጀመር የስልጠና እቅዱን ፤ አመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ አጠቃላይ የውድድር ዘመኑን ሪፖርት የሚያቀርብ አሰልጣኝ የለም፡፡ እንዴት እንዳሸነፈ እና እንዴት ሽንፈት እንዳጋጠመው ማብራርያ የሚሰጥ አሰልጣኝ የለም፡፡ ሪፖርት አቅርቡ ስንላቸው ‹‹ በስራችን ጣልቃ ተገባብን›› እያሉ ያማርሩብናል፡፡ ስለዚህ ይህንን አሰራር መቀየር አለብን፡፡ ቴክኒክ ዳይሬክተሩ እና ፖፓዲች ይህንን የዘልማድ አሰራር በዘመናዊ አሰራር እንዲቀይሩ ነው የቀጠርናቸው፡፡ ››

‹‹ በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የማነበው ነገር ያስገርመኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ከፍ የምናደርገግበት ነገር ከመጠን ያልፋል፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አሰልጣኝ የሚማሩት ነገር አይኖርም፡፡ ይልቁንም ራሱን ያስተምሩታል›› የሚሉ አሉ፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ፈቅ ላላለው እግርኳሳችን ይህንን መናገር አይገባንም፡፡ አሰልጣኙ በትልልቅ ክለቦች ውስጥ በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ስላሳለፈ ብዙ ነገር ያስተምረናል ብለን እናስባለን፡፡ ››

‹‹ የማናውቀው ባህር ውስጥ ገብተናል፡፡ ጭልጥ ብለን ገብተን መውጫው አንዲጠፋን አንፈልግም፡፡ አሰልጣኙ የሚፈልጉትን ተከታትለን ማሟላት ይጠበቅብናል፡፡ በወረቀት ላይ ብቻ ተማምነን ነው ያመጣነው፡፡ በስራቸው መሰረት ታይቶ የኮንትራት ጊዜያቸው ይራዘማል፡፡ ››

‹‹ የውድድር አዘጋጅ አካላት ሁልጊዜም ግራ ያጋቡናል፡፡ ከ17 አመት በታች ውድድር የሚካሄደው በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ስር ነው፡፡ ከ20 አመት በታች ደግሞ በአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር ይካሄዳል፡፡ እኛ እስከ 10 አመት ድረስ ያሉ ታዳጊዎችን ለመያዝ እቅድ አለን፡፡ ነገር ግን ውድድሮች በሌሉበት ሁኔታ ይህንን ማሳካት ከባድ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ጥሩ ተጫዋቾች የት ነው የሚገኙት የሚለውን እያጠናን ነው፡፡ በዚህ በኩል ሌላ ፈተና ይጠብቀናል፡፡ ››

 

 

‹‹ ጥሩ አሰልጣኝ ነኝ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜም እብድ ነኝ፡፡ ›› ደራጋን ፖፓዲች

 

‹‹ እግርኳስ ህይወቴ ነው፡፡ እዚህ ያመጣኝና ከእናንተ ጋር ያገናኘኝም እግርኳስ ነው፡፡ የመጣሁት ለእግርኳሳዊ አላማ በመሆኑ ቡናን ለመርዳት ነው የመጣሁት፡፡ ››

‹‹ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ለጨዋታ አዲስ አበባ መጥቻለሁ፡፡ ስለዚህ ለሃገሪቱ አዲስ አይደለሁም፡፡ ››

‹‹ ጥሩ አሰልጣኝ ነኝ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜም እብድ ነኝ፡፡ ››

‹‹ በሰርቢያ በምጫወትበት ወቅት ክለባችን (ኦኤፍኬ ቤልግሬድ) ከነ ሬድስታር ቤልግሬድ ጋር የሚፎካከር የገንዘብ አቅም አልነበረውም፡፡ በዚህም ምክንያ ተሰጥኦ ላይ ትኩርት ማድረግ ነበረብን፡፡ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች በማጎልበት ለትልልቅ ክለቦች እንሸጥ ነበር፡፡ በዚህም ተመሳሳዩን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተሰጥኦ ቢኖራቸውም ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ አቅም ፣ የአካል ብቃት እና የመሳሰሉትን ሊያሟሉ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ››

‹‹ ከዚህ በፊት የነበሩት የአሰልጣኝነት ዘመኖች ከኋላ ትቻቸው የምሄዳቸው ናቸው፡፡ አሁን ትኩረት የማደርገው ከቡና ጋር ስለሚኖረኝ የውድድር ዘመን ነው፡፡ ››

‹‹ ከ20 አመት በታች እና 17 አመት በታች ቡድኖችን ጨዋታ ተመልክቻለው፡፡ ወደ ዋናው ቡድን የተወሰኑ ተጫዋቾችን ማሳደግም እፈልጋለሁ፡፡ ››

 

 

 

ያጋሩ