የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ለ18 የውድድር ዘመናት ከቆየበት ፕሪምየር ሊግ መውረዱን ተከትሎ እንደ ሌሎች አቻ ክለቦቹ ሁሉ እጣፈንታው መፍረስ ሆኗል፡፡ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፍረስ ለግማሽ ክፍለዘመን ለሚልቅ ጊዜ የኢትዮጵያ እግርኳስን የተቆጣጠረው የድርጅቶች ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፣ የመከላከያ እና የመሳሰሉ ተቋማት የሚያስተዳድሯቸው ክለቦች ፍፃሜ ይበልጥ እየፈጠነ ፣ የከተማ አስተዳደር ክለቦች እና የፋይናንስ ምንጫቸው ከተለያዩ አካላት የሆኑ ክለቦች ደግሞ ይበልጥ እያንሰራሩ መሆኑን ያሳየ ሆኗል፡፡
ተቋማት እና የኢትዮጵያ እግርኳስ
በኢትዮጵያ የመጀመርያው ክለብ እንደሆነ የሚነገርለት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1928 በሁለት ጓደኛሞች ከተመሰረተ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የኮሚዩኒቲ ቡድኖች ጋር ነበር ጨዋታውን የሚያደርገው፡፡ በኋላ ላይ በ1938 ጦር ሰራዊት (አሁን መከላከያ) እና ጠቅል በተቋም ስር የተመሰረቱ የመጀመርያዎቹ ክለቦች መሆን ችለዋል፡፡ በ1953 ደግሞ የመጀመርያው የአገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤት ቡድን የሆነው ኤሌክትሪክ (አሁን ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ሲመሰረት እንደ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ያሉ የፋብሪካ ቡድኖችም ቷቋቋሙ፡፡
እስከ 1945 በአአ (ሸዋ ክፍለሀገር) ክለቦች ብቻ ተገድቦ የነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና (አሁን ፕሪምየር ሊግ) በሁለት ዲቪዝዮን ተከፍሎ ሀገር አቀፍ መልክ ከያዘ ወዲህ በመላ ሀገሪቱ የከተማ መስተዳድር እና የአውራጃ ቡድኖችን ጨምሮ ከ150 በላይ ክለቦች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም ገና በመስፋፋት ላይ በነበረው እግርኳስ ላይ ክለብ ለመመስረት የሚያስችል የፋይናንስ አቅም የነበራቸው ተቋማት ብቻ ነበሩ፡፡ ኤርትራ ጫማ ፣ ኢትዮ ሴሜንት ፣ ምድር ባቡር ፣ ቴሌ ፣ አየር መንገድ ፣ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ እና ንብ (አየር ኃይል) ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ጎሳ እና ብሔርን የሚገልፁ ስሞችን እንዳይጠቀሙ መከልከሉም በአካባቢያዊ ማንነት ከሚመሰረቱ ቡድኖች ይልቅ በድርጅቶች አማካኝነት የሚመሰረቱ ክለቦች እንዲበዙ አድርጓል ተብሎ ይገመታል፡፡
ተቋማት ይበልጥ ወደ እግርኳሱ የገቡበት 1970ዎቹ
የኢትዮጵያ እግርኳስን ከባቢ አየር ከቀየሩ ታሪካዊ ሁነቶች መካከል በ1970ዎቹ አጋማሽ በወቅቱ በተፈጠሩ አዳዲስ ፋብሪካዎች እና ተቋማት ስር ክለቦች እንዲተዳደሩ መደረጉ ነበር፡፡ ይህ አሰራር በርካታ ክለቦች እንዲመሰረቱና የክለብ አደረጃጀታቸው እንደ አዲስ እንዲዋቀር ያደረገ ነበር፡፡ በተቋም ስር የማይተዳደረው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንኳን በወቅቱ በአዲስ ቢራ ፋብሪካ ስር እንዲተዳደር ተደርጎ ነበር፡፡ የፋይናንስ ፣ የንግድ ፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ፋብሪካዎች ስር የሚቋቋሙ ክለቦች እንደ አሸን የፈሉበትም ወቅት ነበር፡፡ ከ1970ዎቹ አጋማሽ እስከ መንስግስት ለውጥ ድረስ በነበሩት አመታትም የኢትዮጵያ ቻምፒየን የሆኑት ክለቦች በሙሉ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት ስር የተመሰረቱ ክለቦች መሆናቸው በድርጅት ሳምባ የሚተነፍሱ ክለቦች በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የነበራቸውን የበላይነት የሚያሳይ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የውድድር አካሄድ ላይ ለውጥ ተደርጎ በአንድ ወጥ የደርሶ መልስ ውድድር አካሄድ በ1990 በአዲስ መልክ ሲጀመር የተሳታፊዎቹ ክለቦች ቁጥር 8 ነበር፡፡ ከነዚህ መካከልም ከኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ በቀር ሌሎቹ ክለቦች በድርጅቶች ቁጥጥር ስር የነበሩ ክለቦች ነበሩ፡፡ በቀጣዮቹ 10 የውድድር ዘመናትም የድርጅት ቡድኖች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቶ አመዛኙን ድርሻ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ ከሚሌንየሙ ወዲህ ግን ቁጥራቸው በአስገራሚ ሁኔታ እየተመናመነ ፣ ለፕሪምየር ሊጉ ብርቅ እየሆኑና ቦታቸውን ለህዝባዊ እና የከተማ አስተዳደር ክለቦች እየተዉ ከኢትዮጵያ እግርኳስ መጥፋታቸውን ተያይዘውታል፡፡ ባለፉት 5 አመታት ብቻ ከእግርኳሱ የወጡት ሙገር ሲሚንቶ ፣ ሐረር ቢራ ፣ ሼር ኢትዮጵያ ፣ ኒያላ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ ሜታ ቢራ ፣ ሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና ዛሬ በይፋ የወንዶቹ ቡድን ማፍረሱ የተረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የመሳሰሉ ክለቦች ስንመለከት በተቋማት ጥላ ስር የሚገኙ ክለቦች ፍፃሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀረበ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ለማስቀመጥ ጥልቅ ጥናት ቢያስፈልግም በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ እየታዩ ካሉ ነገሮች በመነሳት ጥቂት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ማንነት አልባ መሆን
በድርጅት ስም የሚቋቋሙ ክለቦች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ክለቦች በስያሜያቸው አልያም በአካባቢያቸው የሚፈጥሩት ምንም አይነት ስሜት አለመኖሩ በደጋፊ እጦት እንዲሰቃዩ ሲያደርጋቸው ይስተዋላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የከተማ ክለቦች መስፋፋት ደግሞ እነዚህ ደጋፊ አልባ ክለቦች በሜዳ ላይ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ የድርጅት ክለቦች እርስ በእርስ ከሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ውጪ በሌሎች የሜዳም ሆነ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ በከተማ እና ህዝባዊ መሰረት ባላቸው ክለቦች የደጋፊ አድቫንቴጅ ሲወሰድባቸውና ውጤት በማጣት ካሉበት የሊግ እርከን በተደጋጋሚ ሲወርዱ በቅርብ ጊዜያት ያስተዋልነው ጉዳይ ነው፡፡
የድርጅቶች ፍላጎት
ከአንድ ድርጅት በሚገኝ ድጋፍ የሚቋቋሙ ክለቦች ከሚፈተኑባቸው ጉዳዮች መካከል ህልውናቸው በተቋሙ ኃላፊዎች ይሁንታ ላይ የሚንጠለጠል መሆኑ ነው፡፡ ክለቡም ህልውናው በሚመዘገበው ውጤት ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል፡፡ በቅርቡ እንኳን ዳሽን ቢራ እና ሙገር ሲሚንቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸውን ተከትሎ የሚያስተዳድሯቸው ኩባንያዎች ፍላጎት ለማጣት እና ለማፍረስ ተገደዋል፡፡ በሊጉ ከፍተኛ ገንዘብ ከሚመድቡ ክለቦች ተርታ ተሰልፎ የኖረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ዋናው ቡድኑ ውጤት አልባ መሆኑ ክቡን ለማፍረስ እንዳስገደደው በይፋ አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ብልጭ ብለው በአንድ ጀንበር የከሰሙ በርካታ ክለቦችም ከድርጅት ኃላፊዎች ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ድርጅቶች በውጭ ኩንያዎች ቁጥጥር እየሆኑ መምጣታቸው በስሩ የሚገኙትን ክለቦች ሞት ያፋጠነ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ትርፍ በማያስገኙ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት የማይዋጥላቸው መሆናቸው በክለቦች ላይ እንዲጨክኑ አድርጓቸዋል፡፡ ክለብ ከማስተዳደር ይልቅ እግርኳስ ውድድሮችን ስፖንሰር በማድረግ የሚታወቀው ሄኒይከን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሐረር ቢራ ፋብሪካን የግሉ እንዳደረገ የመጀመርያ እርምጃው የሆነው በስሩ የነበረውን ክለብ ለግል ባለሀብት ማዛወር ነበር፡፡ ዲዬጆ የተሰኘው ኩባንያም ከ1970ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የነበረው ሜታ ቢራን አፍርሶታል፡፡ ዳሽን ቢራም እንዲሁ ክለቡን አፍርሶ በእግርኳሱ ዙርያ የሚገኙ ሌሎች ስራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በድርጅት ስር የሚገኙ ክለቦች ደጋፊ አልባ መሆናቸው እና ጉዳዬ ብሎ የሚከታተላቸው የሌለ መሆኑ በእግርኳሱ ምክንያት እየተደረገ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመዘበር በር ይከፍታሉ፡፡ ድርጅቶች በተለምዶ ‹‹ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት›› በሚል ሰበብ ከትርፋቸው ላይ በጀት በመመደብ ክለብ ካቋቋሙ በኋላ አሰራሩን እምብዛም የማይከታተሉ በመሆኑ ይህ ምዝበራ ስር እየሰደደ የድርጅቶቹን ህልውና መፈታተን ጀምሮ ክለቦቻችውን የሚያፈርሱ ተቋማት እየበረከቱ መጥተዋል፡፡
ያደጉ ሃገራት የእግርኳስ አስተሳሰብ ወደ ኢትዮጵያ መግባት መጀመር ሌላው ለድርጅት ቡድኖች መዳከም ተጠቃሽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ተወዳጅ በመሆኑ በእግርኳስ ተጠቅሞ ህብረተሰቡ ጋር ለመድረስ ተቋሞቻችን ለአመታት የተጠቀሙበት መንገድ ክለብ መመስረት ነበር፡፡ በቀደሙት አመታት በርካታ ክለቦች በድርጅት ስም እየተቋቋሙ ውጤታማ በመሆናቸው ድርጅቶቹን ተጠቃሚ ቢያደርግም አሁን አሁን በከተማ ክለቦች እና ህዝባዊ መሰረት ባላቸው ክለቦች እየተዋጡ በመምጣታቸው ክለብ በማስተዳደር ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ ለከፍተኛ የሀብት ብዝበዛ እና ኪሳራ ያጋለጠ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ድርጅቶች የክለብ ባለቤትነትን በመተው ከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ያላቸው ክለቦችን በመጠቀም ድርጅታቸውን ማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደር ክለቦች መስፋፋት
ከ1980ዎቹ ወዲህ ይበልጥ እየተስፋፋ የመጣው የከተማ ክለቦች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሊግ እርከኖች ላይ ከፍተኛውን ቁጥር ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ የከተማ ክለቦች የሚመሰረቱት እና የሚተዳደሩት ከከተማ አስተዳደሩ በሚገኝ ገንዘብ በመሆኑ በአስተዳደራዊ መዋቅራቸው እና ቁመናቸው ከድርጅት ቡድኖች ባይለዩም የአካባቢያዊ ማንነት ያላቸው በመሆኑ የበርካታ ደጋፊ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ የፋይናንስ ምንጮቻቸው እየበዙ መጥተዋል፡፡ ብቸኛ የፋይናንስ ምንጫቸው በከተማ አስተዳደሮቹ ስር አድርገው የተመሰረቱ ክለቦች እንደ ድርጅት ክለቦች ሁሉ ከሚበጀትላቸው በጀት ውጪ የገቢ ምንጮችን ለማበራከት የሚያስችል ቁመና ባይኖራቸውም ካላቸው የደጋፊ አቅም አንጻር በጊዜ ሒደት ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን ማግኘታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከአካባቢያዊ ማንነት ጋር የተያያዙ ክለቦች ከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ምክንያትም አንዳንድ ክለቦች ከደጋፊዎቻቸው በሚሰበሰብ ገንዘብ ገቢያቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ክለቦች መስፋፋትና በእግርኳሱ ላይ የበላይ መሆን የተቋማት ክለቦችን እያዳከመ እንዳለ እየታየ ይገኛል፡፡
የግል ክለቦች እና ህዝባዊ ክለቦች ማበብ
እንደ ከተማ ክለቦች ባይሆንም በግል የሚቋቋቋሙ እና ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ክለቦች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ፋሲል ከተማ በከተማ አስተዳደር ስር የማይገኝ አንጋፋው ክለብ ሲሆን ዋንኛ የፋይናንስ ምንጮቹም ደጋፊዎቹ ናቸው፡፡ በ1928 በጓደኛሞች የተመሰረተውና 1980ዎቹ ወደ ህዝባዊ ክለብነት የተሸጋገረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደጋፊዎቹ መወጮ በተጨማሪ ከ15 በላይ አጋር ኩባንያዎች ያሉት ክለብ ነው፡፡ በተመሰሳይ በጓደኛሞች ተመስርቶ በቡና ገበያ ኮርፖሬሽን ሰር ከተዳደረ በኋላ ወደ ህዝባዊ ክለብነት የተለወጠው ኢትዮጵያ ቡናም ሌላው ከደጋፊዎቹ መዋጮ እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የፋይናስ ምንጭ ያለው ክለብ ነው፡፡ በግለሰብ ተመስርቶ በአሁኑ ሰአት 10 ከሚደርሱ አጋር ኩባንያዎች የገቢ ምንጩን ያደረገው ደደቢት በሊጉ ባለፉት ቅርብ አመታት ተፎካካሪ መሆን ችሏል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ካርታ ላይ የሰፈሩት ወላይታ ድቻ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ጅማ አባ ቡና እና የመሳሰሉት ክለቦች በአሁኑ ሰአት በከተማ አስተዳደር አልያም በድርጅት ስር የማይተዳደሩና ህልናቸው በተለያዩ የገቢ ምንጮች የመሰረቱ ክለቦች ናቸው፡፡
የእነዚህ የፋይናንስ ምንጫቸው ከተለያዩ አካላት ያደረጉ ክለቦች መበራከት በተዘዋዋሪ ኩባንያዎች ክለባቸውን በማፍረስ ወይም ክለብ የመመስረት ሀሳባቸውን በመተው ከእነዚህ ክለቦች ጋር አጋርነት መመስረት ምርጫቸው እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
መጪው ጊዜ
በቀጣዮቹ ጊዜያት በድርጅቶች ሰር የሚገኙ ክለቦች ይበልጥ የሚቸገሩበት ይመስላል፡፡ የከተማ ክለቦች ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ራሳቸውን እያጠናከሩና ይበልጥ የደጋፊያቸውን ቁጥር እያበዙ ይገኛሉ፡፡ ከከተማ አስተዳደር ውጪ የሚገኙ ክለቦችም አብረው የሚሰሩ አጋር ድርጅቶችን ቁጥር በማብዛት በፋይናንስ እየተጠናከሩ እንደመሆናቸው በድርጅት ስር የሚገኙና ውስን የገቢ ምንጭ ያላቸው ክለቦች ላይ ይበልጥ የበላይነታቸውን ማሳየታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በሀገሪቱ እግርኳስ ይበልጥ እየተስፋፋ እና ትኩረት የሚያደርግበት ህዝብም እየጨመረ ከመሄዱ አንጻር ተቋማት ከክለቦች እና ውድድሮች ጋር በአጋርነት ከመስራት ይልቅ ክለብ ያቋቁማሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡