ሲዳማ ቡና አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የክለቡን የ2009 አፈፃጸም ሪፖርት እና የአዲሱ የውድድር አመት እቅድ እና በጀት ይፋ ያደረገበትን ጠቅላላ ጉባኤ ማክሰኞ በሀዋሳ ሮሪ ሆቴል ከረፋዱ 3:00 ጀምሮ አካሂዷል፡፡

ውይይቱን የከፈቱት የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ እና የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ አዱላ በእንኳን ደህና መጣችሁ እና ጉባኤው በመልካም አፈፃፀም እንዲቋጭ ምኞት በማስተላለፍ ነበር፡፡ከአቶ አክሊሉ ንግግር በኃላ በርካታ ውዝግቦችን ያስነሳው የ2009 አፈፃፀም እና 2010 እቅድ ዙርያ በክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሳሳሞ አማካኝነት ሪፓርት ቀርቧል፡፡ አቶ መንግስቱ በሪፖርታቸው በ2009 በአንዳንድ የክለቡን እድገት የማይፈልጉ ግለሰቦች ለዋንጫ ግስጋሴ ላይ የተፈጠረው ውጅንብር ፣ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በአግባቡ አለመሰራት ፣ የወጡት ገንዘቦች ኦዲት አለመደረግ ፣ ወጥ ያልሆነ የአመራር ጉድለት ፣ ከ17 እና 20 አመት በታች ቡድን አለመኖር ፣ የሴቶች ቡድንን አፍርሶ እንደገና መገንባቱ ፣ በ8 አመት የክለቡ ቆይታ የተደራጀ የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር አለመኖሩ ፣ ከታዳጊዎች ይልቅ በርካታ ተጫዋቾችን ከሀገር ውጭ እና ከሀገር ውስጥ ማምጣት ፣ በታዳጊዎች ላይ የፈጠረው አብይ ውዝግብ ያስነሱ የውይይቱ ዋነኛ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

ሲዳማ ቡና በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13 ጨዋታ አሸንፎ ፣ 7 ተሸንፎ ፣ 10 ጨዋታ አቻ በመውጣት በ48 ነጥብ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ እንደ ድክመት የተነሳ ሲሆን በየጊዜው የተጫዋቾች የገንዘብ መጠን መናሩ የክለቡን አቅም መፈታተኑ ፣ የተጫዋቾች ማደሪያ በታሰበለት ጊዜ አለመጠናቀቁ ፣ የገንዘብ አቅም ውስንነት ፣ ተጫዋቾች ከክለቡ እየለቀቁ በየአመቱ አዲስ ቡድን መገንባት ፣ ለዋናው ቡድን ብቻ 16 ሚሊየን ብር በላይ መውጣቱ ፣ የስታዲየም ጥራት ጉድለት ሌሎች በጉባኤው የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ቀጥሎ በቀረበው የ2010 ዕቅድ በስራ አስኪያጁ መንግስቱ ሳሳሞ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን መሆን ፣ ፈርሰው የነበሩትን 17 እና ከ 20 አመት በታች ቡድን አቋቁሞ በሊጎች ላይ ተሳታፊ ማድረግ ፣ ከ14-15 አመት ታዳጊዎች ላይ መስራት ፣ የሴቶቹን እግር ኳስ በይበልጥ ከታች በመስራት ለዋናው ቡድን ማብቃት ፣ የተጫዋቾች ማደሪያን ገንብቶ ማጠናቀቅ ፣ የስታዲየም ደረጃውን ወደ ዘመናዊነት መለወጥ መስራት ፣ ታደጊዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ፣ በሀዋሳ የገቢ ማስገኛ የህንፃ ግንባታ በመገንባት በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባት ፣ በሲዳማ ዞን የታዳጊ እግርኳስ ማሰልጠኛ መክፈት ፣ ደጋፊ ማህበር ማቋቋም እና ሌሎች እቅዶችን በፕሬሬዳንቱ አማካኝነት ቀርበዋል፡፡

ክለቡ ዘንድሮ 9 ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያጣ ሲሆን በምትካቸው 10 ተጫዋቾች (4 ከሀገር ውጭ ፣ 6 ከሀገር ውስጥ) ማስፈረሙን አስታውቋል፡፡ 29 ተጫዋቾች በክለቡ ያሉ ሲሆን 16 ሚሊየን 885 ሺህ 403 ብር ለእነዚህ ተጫዋችች ደሞዝ በድምሩ የሚከፍል ይሆናል፡፡ ለጋናዊው ኬኔዲ አሽሊ የሚከፈለው 174 ሺህ 616 ብር ደግሞ ከፍተኛው ደሞዝ ሆኗል፡፡

ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ልምምዱን የጀመረ ሲሆን በሀዋሳ ኤስ ኦኤስ ሜዳ ልምምዱን እየሰራም ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *