በአራት የእግርኳስ ፌድሬሽኖች አማካኝነት ለ 9 ተከታታይ ቀናት በደቡብ ክልል እና በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 47 የከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ እንዲሁም የታዳጊ ቡድኖች ስለጠና ላይ ለሚሰሩ አሰልጣኞች የአሰልጣኝነት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፣ የጀርመን እግር ኳስ ፌድሬሽን እና የጀርመን ኦሎምፒክ ፅ/ቤት ከሀዋሳ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን ከነሐሴ 23 ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በጀርመናዊው የኢትዮጵያ እና ጀርመን እግር ኳስ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ዩአኪም ፊከርት እና ኢንስራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም አማካኝነት ነበር የተሰጠው፡፡
በስልጠናው የጀርመንን የታዳጊዎች ስልጠና ተሞክሮ በመውሰድ በሜዳና በክፍል ውስጥ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን የታዳጊዎች የግል ብቃት ማጎልበት ፣ የማጥቃት እና የመከላከል አጨዋወት ፣ እድሜን ያማከለ የቦታ አያያዝ ፣ የታክቲክ ፣ ቴክኒክ ፣ የህብረት ስራ እና የመሳሰሉት የስልጠናው አካል ሲሆን ታዳጊ ህፃናትን በመጠቀም በተግባር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ስልጠናውም ዛሬ ሲጠናቀቅ ሰልጣኞቹ በስልጠናው ወቅት ጥሩ አቅም እንዳገኙበት ሲገልፁ ለዮአኪም ፊከርትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ወ/ሚካኤል መስቀሌ እና አቶ አለሙ ኤሮም የሀዋሳ ከተማ ወ/ና ስፓርት መምራያ ኃላፊ እንዲሁም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለስልጠናው ተሳታፊዎች የሰርተፍኬት ሽልማት ሲያበረክቱ ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ለዩአኪም ፊከርትና ለኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም ሽልማት በማበርከት መርሀ ግብሩ ተጠናቋል፡፡