ፊፋ የደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንዲደገም ወሰነ

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ህዳር 2016 በምደብ አራት ፖሎክዋኔ ላይ ሴኔጋልን ያስተናገደችው ደቡብ አፍሪካ 2-1 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ጨዋታው የመሩት ጋናዊው የመሃል ዳኛ ጆሴፍ ላምፕቲ በጨዋታው ላይ ያልተገባ ስራን በመስራታቸው ፊፋ ከእግርኳስ አግዷቸው ነበር፡፡
የፊፋ ዲስፕሊን ኮሚቴ ላምፕቲን እድሜ ልክ ሲያግዳቸው የሴኔጋል እግርኳስ ፌድሬሽን ያልተገባ የዳኝነት ችግር በጨዋታው ላይ ታይቷል በሚል ለካፍ እና ፊፋ ባስገባው ደብዳቤ መሰረት ኮሚቴው በወሰደው ማጣራት ቅጣቱን ሊያስተላልፍ ችሏል፡፡

አሁን ደግሞ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ቢሮ ጨዋታውን እንዲደገም ወስኗል፡፡ የአለምአቀፉ የስፖርት ገላጋዮች ፍርድ ቤት የላምፒቲ ላይ የተወሰነውን ቅጣት መደገፉን ተከትሎ ነው ጨዋታው እንዲደገም የተወሰነው፡፡



በምድብ አራት ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ በነበረው የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫ ቱላኒ ሃልትሻዋዮ ያስቆጠረው የ43ኛ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠበት መንገድ ብዙ አነጋግሯል፡፡ የሴኔጋሉ ተከላካይ ካሊዱ ኩሊባሊ ኳስ ጉልበቱን ብትነካም የመሃል ዳኛው ላምፕቲ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ለባፋና ባፋና ሰጥተዋል፡፡ በጨዋታውም ላይ ላምፕቲ ደካማ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተከትሎ ለቅጣት ተዳርጓል፡፡

በህዳር 2017 ለወደፊት በሚገለፅ ቀን ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል ይጫወታሉ፡፡ ውሳኔው በፊፋ የውድድሮች አዘጋጅ ኮሚቴ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ ከነበራት አራት ነጥብ ወደ አንድ ዝቅ ስትል ሴኔጋል ባለችበት አምስት ነጥብ ትቆያለች፡፡ በጨዋታው የተቆጠሩት ግቦችም አሁን ላይ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ ምድብ አራትን ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርድ በእኩል ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመሩታል፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *