በየአመቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን የሚያሳትፈው የደቡብ ክልል ካስትል ዋንጫ ከመስከረም 6 – 14 በሀዋሳ ይደረጋል፡፡
የደቡብ እግርኳሰ ፌድሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ አራቱ የክልሉ ክለቦች ማለትም ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መሳተፋቸው እርግጥ የሆኑ ክለቦች ሲሆኑ በተጋባዥነት አራት ክለቦች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ አትዮጵያ ቡና ፣ ወልዲያ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ ከተማ የግብዣ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ከነዚህ መካከል በሀዋሳ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ ላይ እንደሚካፈል ለሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም አቶ ወልደሚካኤል ” በአንዳንድ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ይተላለፋል፡፡ እኛ ጥያቄ አቅርበን ገና ምላሽ አላገኘንም፡፡ እስከፊታችን አርብም ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡ እስከ አሁን ግን በተጋባዥነት የሚሳተፉ ክለቦች አልታወቁም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ወልደሚካኤል አክለውም ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ቅድሚያ ፍቃደኛ የሆኑ ከተጠቀሱት ክለቦች ውጭ ቢመጡ በቀዳሚነት ለማሳተፍ እድል እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ለ6 ጊዜ የሚካሄደው ውድድር በካስትል ቢራ ስያሜ ለ5 አመታት ስፓንሰር የተደረገ ሲሆን በድርጅቱ ስያሜ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በዘንድሮው ውድድር ላይ ከሌላው ጊዜ ባማረ መልኩ በማስተናገድ ለኮከቦች በሽልማት መልክ የሚበረከተው የ5000 ሺህ ብር ሽልማት በተወሰነ መልኩ ለማሻሻል መታሰቡ ታውቋል፡፡
የደቡብ ካስትል ዋንጫ ከዚህ ቀደም ከፕሪምየር ሊጉ በተጨማሪ የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ክለቦችን በጋራ የሚያሳትፍ ውድድር የነበረ ቢሆንም ያለፍትን ሶስት አመታት ግን በፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል ብቻ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ለከፍተኛ ሊጉ እና ለአንደኛ ሊጉ ሌላ ውድድር ተዘጋጅቷል፡፡
አምና የተደረገውን ውድድር ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማን በአዲስ ግደይ ሐት-ትሪክ በመታገዝ 3-1 አሸንፎ ቻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡