በኢትዮዽያ እግር ኳስ ታሪክ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ድረስ በጠንካራ ተፎካካሪነቱ እና በርካታ ባለተሰጥኦዎችን በማውጣት ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ የነበረው ኢትዮጵያ መድን ከዝናው በተቃራኒ መንገድ እየተጓዘ በተደጋጋሚ ከፕሪምየር ሊጉ ሲወርድ ከ2005 በኋላም በሊጉ ሳይሳተፍ ቆይቷል፡፡
የክለቡን የቀድሞ ስም ለመመለስ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ከ2009 የውድድር ዘመን አጋማሽ አንስቶ ቡድኑን የተረከቡ ሲሆን ለቀጣይ አመት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎ የአሰልጣኝ አባላታቸውን በመቀየር በምክትል አሰልጣኝነት የቀድሞ የኢትዮዽያ መድን እና የኢትዮዽያ ብሔራዊ ድንቅ አጥቂ ሀሰን በሽር ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ በለጠ ወዳጆን የግብ አሰልጣኝ አድርገዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከነበረው ስብስብ ውስጥ ሚካኤል በየነ ፤ ምናለ በቀለ ፣ ሳምሶን ሙሉጌታ እና ብሩክ ጌታቸው ብቻ ከቡድኑ ጋር ሲቀጥሉ ከ20 በላይ አዲስ ፈራሚዎች እና ታዳጊዎች ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
ከፈረመት ተጫዋቾች መካከል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡-
ወርቀነህ ዲባባ ( ድሬዳዋ ከተማ ) ፣ ተስፋዬ በቃና ( መቐለ ከተማ ) ፣ ፍሬው ብርሃን ( ወልድያ ) አሸናፊ እንዳለ ( አማራ ውሀ ስራ ) ፣ አብርሃም ታምራት ( ወልቂጤ ከተማ ) ፣ ስዑድ ኑር እና ግርማ ፀጋዬ ( ወልዋሎ ) ዮናታን ብርሀነ ( አአ ከተማ ) ፣ አብዱልአዚዝ ዑመር ( ሻሸመኔ ከተማ) ፣ አዳነ አየለ ( አአ ፖሊስ ) ፣ ጊዮን መላኩ ( ሽረ እንዳስላሴ )፣ መሐመድ ሻፊ ( ሚዛን አማን ) ፣ ሀይደር ናስር ( አክሱም ከተማ )፡፡ ከነዚህ ተጫዋቾች በተጨማሪም በጅማ አባ ቡና ለበርካታ ወጣቶች እድል በመስጠት የሚታወቁት አሰልጣኝ ደረጄ በረከት ያሉ ወጣቶችን ወደ ቡድኑ መቀላቀላቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮዽያ መድን ለ2010 የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎ ቅድመ ዝግጅቱን ከባለፈው ሳምንት አንስቶ በቢሸፍቱ ከተማ እያደረገ ይገኛል ።