የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ፍፃሜውን አገኘ

ለ12ኛ ተከታታይ አመት ዕድሜያቸው 14-16 አመት በሚገኙ ታዳጊዎች መካከል ከነሐሴ 4 ቀን ጀምሮ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲከናወን የቆየው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ትላንት ጀሞ በሚገኘው የዶን ቦስኮ ሜዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ አመራር ፣ የክለቡ ደጋፊዎች እና በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በታደሙበት በድምቀት ፍፃሜውን አግኝቷል።

የመጫወት ልምድ ያላገኙ ታዳጊዎች በተሰኘው ምድብ ድል ስፖርት እና ፒጂኤስን ባገናኘው ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በመለያየታቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ፒጂኤስ 3-2 በማሸነፍ የዋንጫው አሸናፊ ሆኗል።

በመቀጠል የመጫወት ልምድ ባገኙ ምድብ ጫካ ሜዳ እና ኤስዋይጂ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ጠንካራ የመሸናነፍ ፉክክር ታይቶበት መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ጫካ ሜዳዎች በግብ ጠበቂያቸው ጥንካሬ ታግዘው 4-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።

ከጨዋታዎቹ ፍፃሜ በኋላ ወደ ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርአት ያመራ ሲሆን በዚህ መሰረት በሁለቱም ምድብ ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት ቡድኖች የሜዳልያ ፣ ለእያንዳንዳቸው ቡድኖች አምስት የመጫወቻ ኳስ ከነ ሙሉ የተጨዋቾች ትጥቅ ሲበረከትላቸው የውድድሩ አሸናፊዎች ለሆኑት ጫካ ሜዳ እና ፒጂኤስ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመቀጠል ኮከቦች ሽልማት ሲከናወን የመጫወት ልምድ ባላገኙት ምድብ በኮከብ ተጨዋችነት ይበልጣል ቻሌ ከድል ስፖርት ፣ በኮከብ ጎል አስቆጣሪነት ኄኖክ ፍቅሬ በ9 ጎል ፒጂኤስ ፣
ኮከብ አሰልጣኝ ሐብታሙ መለሰ ከፒጂኤስ ሆነዋል።

የመጫወት እድል ባገኙ ምድብ የኮከቦች ሽልማት ደግሞ በኮከብ ተጨዋችነት አሸናፊ ሞሼ ከጫካ ሜዳ ፣ በኮከብ ጎል አስቆጣሪነት በ7 ጎል አማረ ሰለሞን ከጫካ ሜዳ ፣ በኮከብ አሰልጣኝነት ትጓደድ ምንውየለት በመሆን ተመርጣለች።

ለአንድ ወር በቆየው በዚህ የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ወድድር ወጥ አቋማቸውን በማሳየት የብዙ የስፖርት ቤተሰቡን በጥሩ እንቅስቃሴያቸው ማሳመን የቻሉ በርካታ ታዳጊዎችን ለማየት የቻልን ቢሆንም በተለይ እነዚህ በፎቶ የምትመለከቷቸው ታዳጊዎች ልዩ ነበሩ።

የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ለ12 ተከታታይ አመት ሲዘጋጅ በርካታ ለክለብ ፣ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻሉ ተጨዋቾችን እያፈራ የሚገኝ በመሆኑ ሁሌም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልክታችንን እያስተላለፍን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ማህበር ይህን ውድድር በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ አድርጎ ከመሰየሙ ባሻገር ይህን የውድድር እድል ለታዳጊዎች በመፍጠሩ ሊመሰገን ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *