ባለፈው ሳምንት የሊጉ አሸናፊ ከሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ምን እንደሚመስል በአዳማ ከተማ በመገኘት አቅርበን እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በቀጣይነት በተከታታይ የሌሎች ክለቦችን የቅድመ ውውድር ዝግጅታቸውን እንደምናቀርብ በገለፅነው መሰረት ዛሬ የአዳማ ከተማ የዝግጅት እንቅስቃሴን እንዲህ አሰናድተን አቅርበነዋል።
በ2005 ከፕሪምየር ሊግ ወርዶ ዳግም 2007 ከተመለሰ በኋላ ለተከታታይ 3 አመታት 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በሊጉ አንጻራዊ ወጥ አቋም ካሳዩ ክለቦች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ በተለይ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎችን አመዛኙን በማሸነፍ በሜዳው የማይቀመስ ቡድን ሆኖ ዘልቋል።
በ2009 የውድድር አመት ከሰላሳ ጨዋታ አስራ ሦስቱን ጨዋታ በድል ተወጥቶ ፣ በአምስቱ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ ፣ በአስራ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ ፣ 27 ጎል በተቃራኒ ቡድን መረብ ላይ አሳርፎ ፣ 17 ጎል ተቆጥሮበታል፡፡ በዚህም መሰረት በ51 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ሊያጠናቅቅ ችሏል ።
አዳማ ከተማ እንደ ጥንካሬ የሚነገርለት በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በድል የሚወጣ መሆኑና ከታች ከታዳጊ ቡድኑ ተጨዋቾችን በማሳዳግ ያለፉትን አመታት ስኬታማ የሆነ ቡድን ቢሆንም የዛኑ ያህል በርከት ያሉ በሊጉ ጥሩ ብቃታቸውን ያሳዩ ተጨዋቾችን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክለቦችና ከአፍሪካ ሀገራት ወደ ክለቡ በማምጣት ቡድኑን በመገንባት ይታወቃል።
አዳማ ከተማ ከ2009 ስብስቡ ውስጥ መክብብ ደገፉ (ግብ ጠባቂ) ፣ ብሩክ ቀልቦሬ ፣ ፋሲካ አስፋው ፣ ቢንያም አየለ ፣ እሸቱ መና እና ሞገስ ታደሰ ጋር የተለያየ ሲሆን ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ( አአ ከተማ ) ፣ ተከላካዩ አዳርጋቸው ይላቅ ( ቅዱስ ጊዮርጊስ ) ፣ አማካዮቹ ከንአን ማርክነህ ( አአ ከተማ ) እና አብዱልላኪም ሱልጣን ( ኢትዮ ኤሌትሪክ) እንዲሁም አጥቂው አላዛር ፋሲካ ( ወላይታ ድቻ) ለክለቡ የፈረሙ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ከአዲሶቹ ፈራሚዎች በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን አንድ አጥቂ አስመጥቶ እየሞከረ ይገኛል።
በዘንድሮ ከ20 አመት በታች ቡድን ውስጥ መልካም የሚባል የውድድር ዘመን ያሳለፉት መናፍ አወል ፣ ፉአድ ፈረጃ እና እዮብ ማቲዮስ ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
23 ተጨዋቾችን ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ በአዳማ ከተማ በአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ እየተመራ በቀን ሁለት ጊዜ የልምምድ መርሀ ግብር ዝግጅታቸውን አጠናክረው እየሰራ ይገኛል። በዝግጅት ወቅት ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ ሙጂብ ቃሲም በእረፍት እና በጉዳት ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅት ያልጀመሩ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
ክለቡ በቀጣይነት ስለሚኖረው እቅድ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ለማናገር ያደረግነው ጥረት ካለ ቢሮ ኃላፊዎች ፍቃድ አስተያየት አልሰጥም የሚል ምላሽ በመስጠታቸው ምክንያት ሳይሳካ የቀረ ቢሆንም የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየው በሰጡን ምላሽ ብዙም ወደ ገቢያው እንደማይገቡና አንድ ተጨዋች ከሀገር ውስጥ አብዛኛው ነገር ከስምምነት ደርሰው በአንድ ጉዳይ ብቻ እንዳልተጠናቀቀ ገልፀው። ከኢትዮዽያ ውጭ ግን ሦስት ተጨዋቾች በቅርብ ጊዚያት በማምጣት የሙከራ ጊዜ በመስጠት በሚያሳዩት እንቅስቃሴ ሊያስፈርም እንደሚችል አሳውቀው ስማቸው ከአዳማ ከተማ ጋር በስፋት እየተነሳ የሚገኘው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ሊመለሱ ይችላል ስለተባለው ጭምጭምታ ምንም የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ እና ክለቡ ባሉት አሰልጣኞች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ሆኖም ሶከር ኢትዮዽያ ለጉዳዩ ቅርበት ባላቸው አካላት ባገኘችው መረጃ መሰረት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ጋር አብረው እንደማይቀጥሉ እና ከሞሮኮ ስልጠና ሲመለሱ አዳማ ከተማን በይፋ ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።