ቅዱስ ጊዮርጊስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፖርቱጋላዊው ካርሎስ ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ አድሮጎ መሾሙን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡

ሆላንዳዊው ማርቲን ኩፕማንን ተክለው ያለፉትን ሁለት የውድድር አመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፉት አሰልጣኝ ማርት ኑይ በጤና እክል ምክንያት ከክለቡ የእለት ተእለት ስራ ከተገለሉ ከ4 ወራት በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን የውድድር ዘመኑንም የማርት ኑይ ረዳት የሆኑት ዘሪሁን ሸንገታ እና ፋሲል ተካልኝ ቡድኑን እየመሩ ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡

ፈረሰኞቹ ከአሰልጣኝ ማርት ኑይ ጋር እንደማይቀጥሉ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ቀጣዩ አሰልጣኝ ማንነት ሲያነጋግር ቆይቶ ከክለቡ ጋር ያለፉትን ሳምንታት ስማቸው ሲያያዝ የነበሩት ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡

በፖርቱጋሏ ፔናላቫ ዶ ካስቴሎ የተወለዱት የ43 አመቱ አሰልጣኝ የቀድሞዋ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ወደሆነችው አንጎላ በ2014 ከመጡ በኋላ የሀገሪቱ ታላላቄ ክለቦች በሆኑት ሪክሬቲቮ ዳ ካላ እና ሪክሬቲቮ ዶ ሊቦሎ አሰልጣኝነት አሳልፈዋል፡፡

ከ1996 ጀምሮ የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ መቅጠር ያቆመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት 15 አመታት የሆላንድ ፣ ሰርቢያ ፣ ቦስኒያ ፣ ጣልያን ፣ ጀርመን ፣ ብራዚል እና ፖርቱጋል ዜግነት ያላቸው አሰልጣኞች ቀጥሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *