ከናጅራን የተለያየው ዋሊድ ለአል ካሊጅ ለመጫወት ተስማምቷል

ኢትዮጵያዊው የመሃል ተከላካይ ዋሊድ አታ ከሳውዲ አረቢያው ናጅራን ስፖርት ክለብ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ሌላኛው የሳውዲ ክለብ አል ካሊጅ ማምራቱ ተረጋግጧል፡፡ ዋሊድ በኖርዌይ ሊግ ለሚወዳደረው ሶግንዳል በውሰት ያለፉትን አራት ወራት ካሳለፈ በኃላ ከናጅራን ጋር የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም ከክለቡ መለያየትን ምርጫው አድርጓል፡፡

የቀድሞው የኤአይኬ፣ ቢኬ ሃከን እና ዳይናሞ ዛግሬብ ተጫዋች በናጅራን መጫወት ሳይችል ከክለቡ መለያየቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ዋሊድ አል ካሊጅን ከወዲሁ የተቀላቀለ ሲሆን ከናጅራን የለቀቀበትን ምክንያት ለሶከር ኢትዮጵያ በተለይ ገልጿል፡፡ “ከናጅራን ጋር የነበረኝ ውል በስምምነት ፈርሷል፡፡ ክለብ የቀየርኩት በናጅራን ባለው ከፍተኛ የውስጥ ችግር ነው፡፡” ሲል ዋሊድ አስረድቷል፡፡
አል ካሊጅ ለዋሊድ የምን ያህል ግዜ ውል እንዳስፈረመው ባይጠቆምም ተጫዋቹ ቢያንስ የአንድ ዓመት ውል ሳይፈርም እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ አል ካሊጅ በ2016/17 ከአብዱላቲፍ ጃሜል ሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ በ23 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ሊወርድ ችሏል፡፡ አል ካሊጅ በቀጣይ አመት በሳውዲ አንደኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደር ሲሆን ዳግም ወደ ዋናው ሊግ በፍጥነት ለመመለስ አልሟል፡፡

ከ2007 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ጀምሮ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተወሰኑ ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለው የቀድሞ ስዊድን ከ21 ዓመት በታች ኢንተርናሽናል ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ለስድስት ክለቦች ተጫውቷል፡፡ ዋሊድ በአንድ ክለብ ሰፋ ያለ ግዜ ለመቆየት እየተቸገረ ሲገኝ ከቢኬ ሃከን ቆይታው በኃላ በኦስተርሰንድስ መልካም የሚባል ግዜን አሳልፏል፡፡

Leave a Reply