በሴንትራል ሆቴል ባለቤት ወ/ሮ አማረች ዘለቀ መስራችነት እና ስፖንሰር አድራጊነት በየአመቱ በክረምት ወራት የሚካሄደው የሴንትራል መለስ ዋንጫ የታዳጊዎች የእግርኳስ ውድድር ዘንድሮም ለ9ኛ ጊዜ ከሐምሌ 12 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ እሁድ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በሁለት የእድሜ እርከኖች እና በሁለቱም ጾታዎች በተካሄደው የዘንድሮው ውድድር በወንዶች ከ13 አመት ዕድሜ በታች ታዳጊዎች 24 ቡድኖች ፣ ከ15 አመት ዕድሜ በታች ታዳጊዎች 32 ቡድኖች ሲካፈሉ በታዳጊ ሴቶች 6 ቡድኖችን ጨምሮ በድምሩ 62 ክለቦች ተሳትፈውበታል፡፡
አስቀድሞ ከ13 አመት በታች ወንዶች በዳንኤል ዋለልኝ እና ህይወት ብርሃን መካከል በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት ህይወት ብርሃን 7-6 በማሸነፍ የውድድሩ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
በማስቀጠል በተካሄደው ከ15 አመት በታች ታዳጊዎች የፍፃሜ ጨዋታ ዛማ አካዳሚ ከ አብርሽ ፕሮጀክት በተመሳሳይ በመደበኛ ክፍለጊዜ ያለ ግብ በአቻ ውጤት በመጠናቃቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት አብርሽ ፕሮጀክት 5-4 በሆነ ውጤት አሸንፎ የተዘጋጀውን ዋንጫ አንስቷል።
በሴቶች የፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት ሀዋሳ ከተማ ቢ ከ የነገው ተስፋ ሲሆኑ በጨወታውም ሀዋሳ ከተማ ቢ 2-1 አሸናፎ በሴቶች ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን ዋንጫ አንስቷል ።
በርካታ ተጫዋቾች እየፈሩበት እንደሆነ የሚታወቀው የሴንትራል መለስ ዋንጫን ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ ክለቦች በመከታተል ታዳጊዎችን እየመለመሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ማሳያው የሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድኑ በየአመቱ በሚሳተፍበት ውድድር ውጤታማ የሚሆነው በዚህ ውድድር ላይ የሚገኙ በታዳጊዎችን በመልመል እንደሆነ ይታወቃል።
በየአመቱ የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ የሚገኘው ይህ የታዳጊዎች ውድድር ለተከታታይ አመት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ያለው ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል አስተዋጽኦ አድናቆት የሚቸረው ነው፡፡