ቅድመ ውድድር ዝግጅት – መከለከያ

ጦረኞቹ በአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው በተሾሙት አሰልጣኝ ምንያምር ጸጋዬ እየተመሩ በቢሸፍቱ ከተማ አየር ኃይል ሜዳ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች በተገኙበት በቀን ሁለት ጊዜ ጠንካራ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ ።

በኢትዮዽያ እግር ኳስ ታሪክ ከሚጠቀሱ አንጋፋ ፣ በደጋፊ እና በውጤት ያሸበረቀ ታሪክ ካላቸው ክለቦች መካከል የሚጠቀሰው የቀድሞው መቻል ያለፉትን አመታት በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚዋልል ቡድን ሆኗል፡፡ መከላከያ በ2009 የውድድር አመት የተሳካ ጊዜ ያላሳለፈ ሲሆን ከካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ ተሸንፎ በቅድመ ማጣርያው ዙር ሲሰናበት በጥሎ ማለፉም በፍጻሜው በወላይታ ድቻ ተሸንፎ ለ3ኛ ተከታታይ አመተት በአፍሪካ ውድድር የመሳተፍ እድሉን አምክኗል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ ደግሞ በአመቱ ካደረጋቸው 30 ጨዋታዎች 8 አሸንፎ ፣ 9 ተሸንፎ ፣ 13 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 24 ጎሎች አስቆጥሮ 35 ጎል ተቆጥሮበት በ37 ነጥብ 8ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

በዘንድሮው ክረምት ገብያው ላይ የተቀዛቀዘው መከላከያ ከጥቂት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቶ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ አስፈርሟል፡፡ ከቡድኑ ጋር አብረው የማይቀጥሉ ተጨዋቾች ሙሉጌታ ደሳለኝ (ግብ ጠባቂ) ፣ ሚልዮን በየነ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ባዬ ገዛኸኝ ሲሆኑ ወደ ክለቡ የተቀላቀሉት አዲስ ተጨዋቾች አማኑኤል ተሾመ ( አማካይ/ ወላይታ ድቻ ) እና አቅሌሲያ ግርማ ( አጥቂ / ጅማ ከተማ ) ናቸው። ከቡድኑ ነባር ተጨዋቾች ውስጥም ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ አዲስ ተስፋዬ ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ታፈሰ ሰርካ ለተጨማሪ ሁለት አመታት ኮንትራታቸውን አራዝመዋል፡፡ በውጪ ተጫዋቾች ዝውውር በተሟሟቀው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮትም የውጭ ተጫዋች በቡድኑ ያላካተተ የፕሪምየር ሊጉ ብቸኛው ክለብ ሆኗል፡፡

ጦሩ ከታች ከተስፋው ቡድኑ ሦስት ተጨዋቾችን ያሳደገ ሲሆን ለመከላከያ ከታች ያደጉት ሙሉ ስም ፖል ኦዱሎ (ግብ ጠባቂ) ፣ አቤል ከበደ እና አብነት ይግለጡ ናቸው።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ምንያምር ጸጋዬ ስለ ክለቡ የዝግጅት ቆይታ እና ስለ ውድድር አመቱ በሰጡት አስተያየት ባላቸው ስብስብ የተሻለ የውድድር ዘመን እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡

” ዝግጅታችንን ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እየሰራን እንገኛለን፡፡ አምና በፕሪምየር ሊጉ እንደችግር የወሰድነው ብዛት ያላቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቃችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምንፈልገውን ያህል ብዙ ርቀት እንዳንጓዝ ክፍተት ፈጥሮብናል፡፡ ከዚህ በመነሳት የተሻለ የውድድር ጊዜ ለማሳለፍ እየሰራን እንገኛለን።
” በቡድናችን ውስጥ የነበሩት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ውል ያላቸው ሲሆን ውላቸው የተጠናቀቀ ወሳኝ ተጫዎቻችንን ውል አድሰናል፡፡ ከታዳጊ ቡድናችንም ሦስት ተጨዋቾች ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ ታዳጊዎችን እየተካን መሄድ ስላለብን ይህን አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ ቡድናችን ብዙ አልተነካካም፡፡ ባለን ነገር የተሻለ ነገር ሰርተን ውጤታማ ለመሆን እንሰራለን” ብለዋል ።

ከመከላከያ ክለብ ጋር ተያየዞ አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከክለቡ የረጅም ጊዜ ተጨዋች መሆን ያገለገለው አምበሉ ሚካኤል ደስታ ከክለቡ ጋር ውል በማፍረስ ወደ ሌላ መቐለ ክለብ ሊያመራ እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን ይህ እውን የሚሆን ከሆነ በምትኩ ሌላ ተጨዋች ሊያመጡ እንደሆነ ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪም የክለቡ ወሳኝ ተከላካይ የሆነው አዲስ ተስፋዬ ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ እስካሁን ያላገገመ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ወራትም ከሜዳ ይርቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መከላከያ የክለቡን ወቅታዊ አቋም ለመፈተሽ ይረዳው ዘንድ መስከረም 20 ይጀምራል ተብሎ እየተጠበቀ ባለው የአአ ከተማ ዋንጫ ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *