ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በዛው በሀዋሳ ክለቡ ለራሱ ባስገነባው ሰው ሰራሽ ሜዳ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በ1990 በአዲስ አቀራረብ መካሄድ ከጀመረ በኋላ የመጀመርያው እና ብቸኛው የሊጉ አሸናፊ የሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኝ ክለብ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ባለፉት ጥቂት አመታት ከሚጠበቅበት በታች የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ሆኗል፡፡

በ2009 የውድድር አመት ያስመዘገበውን ውጤት ስንመለከት ብዙ ጎል የሚያስቆጥር መሆኑ ጠንካራ ጎኑ ቢሆንም በርካታ ጎሎች የሚቆጠርበት እና ብዛት ባለው ጨዋታ ሽንፈት በማስተናገድ ከሚጠቀሱት ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ካደረጋቸው 30 ጨዋታዎች 9 አሸንፎ ፣ 13 ተሸንፎ ፣ 8 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 35 ጎል አስቆጥሮ ፣ 37 ጎሎች ተቆጥረውበት በ35 ነጥብ 10ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

ለ2010 የውድድር አመቱን የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዝግጅቱን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ 33 ተጨዋቾችን በመያዝ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ያቡን ዊልያም ፣ አስጨናቂ ሉቃስ ፣ እስራኤል በጉዳት ምክንያት ልምምድ ላይ ያልተሳተፉ ተጨዋቾች ናቸው።

በዘንደሮ የውድድር አመት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አብረው የማይቀጥሉ ተጨዋቾች ጋዲሳ መብራቴ ፣ ኃይማኖት ወርቁ ፣ ዮናታን ከበደ ፣ ጃኮ አራፋት ፣ ለይኩን መርዶክዮስ ፣ ምስግናው ወልደ ዮሐንስ ፣ ተስፋ ኤልያስ ፣ መስፍን ሙዜ እና ወንድሜነህ አይናለም ሲሆኑ ተክለማርየም ሻንቆ (ግብጠባቂ/ አአ ከተማ ) ፣ ሳዲቅ ሴቾ ( አጥቂ /ኢትዮ ቡና ) / ፍቅረኢየሱስ ተወልደ ብርሀን ( አጥቂ / ንግድ ባንክ ) ፣ ዳዊት ፍቃዱ ( አጥቂ / ደደቢት ) ፣ ጅብሪል ( አማካይ ንግድ ባንክ ) ፣ ያቡን ዊልያም ( አጥቂ / ኢትዮ ቡና) ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በየአመቱ ከወጣት እና ታዳጊ ቡድኑ ተጫዋች በማሳደግ ሰፋ ያለ እድል በመስጠት የሚታወቀው ሀዋሳ ከተማ ለ9 የተስፋ ቡድኑ ተጨዋቾች የሙከራ ጊዜ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን እነሱም ሚካኤል ልዑልሰገድ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ወንድማገኝ ታደሰ ፣ ጌትነት ቶማስ ፣ ጸጋጋብ ዮሴፍ ፣ ዳግም ተፈራ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ ገብረመስቀል ዱባላ እና ቸርነት አውሽ ናቸው። ከነዚህ ተጨዋቾች መካከል በእንቅስቃሴያቸው አሰልጣኞቹን ማሳመን የቻሉ አምስት ተጨዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ሊያድጉ እንደሚችሉ ታውቋል።

ቡድኑ ውስጥ የሙከራ ጊዜ እየተሰጠው ያለው አንጋፋው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሙሉአለም ረጋሳ ሙከራውን በተሳካ ሁኔታ እያደረገ እንደሆነ ከክለቡ አካባቢ የሰማን ሲሆን በዚህ እንቅስቃሴው የሚቀጥል ከሆነም ለሀዋሳ ከተማ ሊፈርም ይችላል ተብሎ ይጠበቃል ።

በዝግጅታቸው ወቅት በአሰልጣኝ አባላቶቹ ታግዘው ልምምዳቸውን እየሰሩ የሚገኙት ሀዋሳዎች በሚታወቁበት ኳስን መስርቶ በፈጣን እንቅስቃሴ የጎል እድል መፍጠር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠትም ሆነ በጨዋታ ላይ ቡድኑን እንዳይመሩ በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ6 ወራት ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑን ተከትሎ ስለ ቡድኑ ዝግጅት ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ቆይታ ያደረገው ምክትል አሰልጣኙ ሙሉጌታ ምህረት የቡድኑ ችግር የነበረውን ልምድ ያላቸው ተጫዋቾትን እጥረት ለመቅረፍ እንደተንቀሳቀሱ ገልጿል፡፡ ” በ2009 ብዙ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ በዋናነት ቡድኑን መምራት የሚችል ልምድ ያለው ተጨዋች አለመኖር እና ከታች የመጡት ታዳጊ ተጨዋቾች በፍጥነት ከቡድኑ ጋር አለመዋሀድ የቡድናችን መሰረታዊ ችግር ነበረ። ዘንድሮ ከዚህ ስህተታችን በመነሳት ልምድ ያላቸው ጨዋታን መቆጣጠር የሚችሉ ተጨዋቾችን አምጥተናል፡፡ አስበናቸው ሳናመጣቸው የቀሩ ተጫዋቾች ቢኖሩም የተሻለ ቡድን ዘንድሮ እናያለን ብዬ አስባለው። ” ብሏል፡፡

በ2009 ሀዋሳ ምርጥ በማጥቃቱ ረገድ ምርጡ ቡድን እንደነበር ብዙዎች ቢስማሙበትም በመከላከል ላይ የነበረው ችግር ዋጋ ሲያስከፍለው ተስተውሏል፡፡ ክለቡም ይህን ተረድቶ ድክመቱን የማሻሻል ስራ እየሰራ መሆኑን ሙሉጌታ ይናገራል፡፡ ” ብዙ ጎሎች ተቆጥረውብናል ፡፡ ቅድም እንዳልኩት ከታች በመጡት ታዳጊዎች እና በነባሮቹ መካከል በተለይ አንደኛው ዙር ላይ የመናበብ ችግር ነበር፡፡ ዘንድሮ ብዙ ጎል እንዳይቆጠርብን ይህን ለማስተካከል እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ሀዋሳ ከተማ በአካባቢው ከሚገኙ የተለያዩ ታዳጊ ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እያደረገ ሲሆን መስከረም 13 በሚጀምረው የደቡብ ክልል ካስትል ካፕ ተሳታፊ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *