በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ከሱፐርስፖርት ዩናይትድ ጋር ካለግብ አቻ ተለያይቶ ለመልሱ ጨዋታ የተሻለ እድልን ይዞ ተመልሷል፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገው ጨዋታ እንግዳው ዜስኮ በግብ ሙከራ ከተጋጣሚው ልቆ ታይቷል፡፡
ሱፐርስፖርት በጨዋታው መልካም አጀማመር ያሳየ ሲሆን በ14ኛው ደቂቃ ብራድሊ ግሎብለር አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ቢችልም ግቡ ከመቆጠሩ በፊት ኳስ በእጅ በመነካቱ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ የሰሜን ዛምቢያ ክለብ የሆነው ዜስኮ በበኩሉ ከ30ኛው ደቂቃ በኃላ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን በጄሲ ዌሬ አማካኝነት ቢፈጥሩም የሱፐርስፖርቱ ሮንዌን ዊሊያምስ አምክኗቸዋል፡፡
በሁለተኛው 45 ዜስኮ ተጠናክሮ ሲቀርብ በተደጋጋሚ በማጥቃቱ ወረዳ ላይ ቢደርሱም በሚወስዷቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች ምክንያት ወሳኝ የሆነ ከሜዳ ውጪ ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም፡፡ ሜይቢን ካሌንጎ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሲመክን ግብ ጠባቂው ዊሊያምስን የጆን ቺካንዱን ወሳኝ ሙከራ ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ ሳምንት በሰሜን ዛምቢያ በምትገኘው ንዶላ ከተማ ይደረጋል፡፡ ዜስኮ ከሜዳው ውጪ ካሳየው አቋም እና በሜዳ ለተጋጣሚዎቹ ፈታኝ ከመሆኑ አንፃር ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ እድሉ የሰፋ መስሏል፡፡ አመቱ ለዜስኮ መልካም የሚባል ሲሆን በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የተሻለ ጉዞ ላይ ሲገኝ በኤምቲኤን ፋዝ ሱፐር ሊግ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ከመሪው ግሪን ቡፋሎስ በ5 ነጥቦች ብቻ ተለያይቶ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የአርብ ውጤት
ሱፐርስፖርት ዩናትድ 0-0 ዜስኮ ዩናይትድ
የዛሬ ጨዋታዎች
20፡00 – አል ሂላል ኦባያድ ከ ቲፒ ማዜምቤ (ኦባያድ ስታዲየም)
20፡30 – ፋት ዩኒየን ስፖርት ከ ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን (ኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃሰን)
20፡45 – ሞሊዲያ ክለብ ደ አልጀር ከ ክለብ አፍሪካ (ስታደ ጁላይ 5 1962)