ቻምፒየንስ ሊግ፡ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ አሃሊ ከኤስፔራንስ ትኩረትን ስቧል

በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምሩ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ አል አሃሊ እና ኤስፔራንስ የሚገናኙበት ጨዋታ ሰፊ ግምትን ሲያገኝ የሞዛምቢኩ ፌሮቫያሪዮ ቤይራ ዩኤስኤም አልጀርን ዛሬ ከሰዓት ያስተናግዳል፡፡

የአህጉሪቱ ታላቅ የክለቦች ውድድር በሆነው ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ግዜ 16 ክለቦች ከተሳተፉበት የምድብ ግጥሚያ በኃላ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ሁለት የቀድሞ ቻምፒዮኖችን የሚያገናኘው የአል አሃሊ እና ኤስፔራንስ ጨዋታ የብዙዎችን ቀልብ ከወዲሁ መሳብ የቻለ ነው፡፡ አል አሃሊ የግብፅ ሊግን አሁንም በአሳማኝ በሆነ ሁኔታ ያሸነፈ ሲሆን ኤስፔራንስ በበኩሉ የቱኒዚያ ሊግ 1ን ግብፅ ካስተናገደችው የአረብ ሃገራት ቻምፒየንስ ሊግ ጭምር ቻምፒዮን በመሆን ጠንካራ ክለብ መሆኑን አስመክሯል፡፡

ሁለቱም ክለቦች ከ2014 ወዲህ በቻምፒየንስ ሊግ ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችሉ ቢቆዩም በ2017ቱ ውድድር ግን የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ አል አሃሊ የደቡብ አፍሪካውን ኦርላንዶ ፓይሬትስን በ2013 እንዲሁም ኤስፔራንስ የሞሮኮውን ዋይዳድ ካዛብላንካን በ2011 ፍፃሜ ከረቱ በኃላ ዋንጫው ማንሳት አልቻሉም፡፡ አል አሃሊ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሊግ የተዛወረውን የአምበሉን ሆሳም ጋሃሊ ግልጋሎት ሲያጣ ለቤድቬስት ዊትስ ለመጫወት ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው አምር ገማልም ከቡድኑ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በፋውዚ ቤንዛርቲ የሚመራው ኤስፔራንስ በሊጉ ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እየመራ ሲገኝ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ፣ ፋክረዲን ቤንየሱፍ፣ ቻላሊ እና አንሲ ባድሪ በጥሩ ብቃት ላይ መገኘታቸው ከጨዋታው የተሻለ ነገር እንዲጠብቅ ያስችለዋል፡፡

ቤይራ ላይ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ የአልጄሪያውን ዩኤስኤም አልጀርን ይገጥማል፡፡ የሱዳኖቹ አል ሂላል እና አል ሜሪክ በሱዳን እግርኳስ ፌድሬሽን እገዳ ምክንያት ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ ሲሆን በተፈጠረለት እድል ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈው ቤይራ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የተሻለ ሪከርድን ይዟል፡፡ ቤይራ በሜዳ ጠንካራ ቡድን ሲሆን የሰሜን አፍሪካ ተጋጣሚዎችን ቢያንስ በጠባብ ውጤት ሲያሸንፍ ይታያል ነገር ግን ክለቡ ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር ችግር እንዳለበት በምድብ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 3 ግቦች ምስክር ናቸው፡፡ በአልጄሪያ ሊግ 1 አምና ቻምፒዮን መሆን ሳይችል በሶስተኛ ደረጃነት ያጠናቀቀው ዩኤስኤም አልጀር የተወሰኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በዝውውር መስኮቱ ቢያጣም ከሞዛምቢክ ተጋጣሚው የተሻ ለአፍሪካ የክለቦች ውድድር ልምድ ስላለው የማለፍ ቅድመ ግምቱን አግኝቷል፡፡ ዩኤስኤም አልጀር ከሜዳው ውጪ በምድብ ጨዋታዎች ያደረጋቸውን ግጥሚያዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ወደ ዚምባቡዌም አቅንቶ በካፕስ ዩናይትድ መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ቤይራን በበኩሉ ከሜዳው ውጪ በምድብ ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሷል፡፡

የቻምፒየንስ ሊጉን ከፍተኛ ግብ አገቢነት አሁንም የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላዲን ሰዒድ በ7 ሲመራ የአል አሃሊ ትሪፖሊው ሞአድ ኤላፊ እና የአል ሜሪኩ ባክሪ አል መዲና በ6 ይከተላሉ፡፡ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ ከኤስፔራንስ 5 ግብ አለው፡፡ ኤላፊ እና ኬኔሲ ክለቦቻቸው አሁንም በውድድር ላይ ስለሚገኙ ከሳላዲን ጋር የግብ መጠናቸው የማስተካከል ይሁን የመብለጥ እድል አላቸው፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች
15፡00 – ክለብ ፌሬቫያሪዮ ደ ቤይራ ከ ዩኤስኤም አልጀር (ኢስታዲዮ ዶ ቺቬቬ)
19፡00 – አል አሃሊ ከ ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)

የእሁድ ጨዋታዎች
15፡00 – ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሉካስ ማስተርፒስስ ሞሪፔ ስታዲየም)
20፡00 – አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *