ያለፉትን አመታት ላለመውረድ እየተጫወተ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌትሪክ በሀዋሳ ከተማ ታደሰ እንጆሪ ሆቴል መቀመጫውን በማድረግ በም/አሰልጣኝ ኤርምያስ ተፈሪ እየተመራ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።
የ3 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ኤሌክትሪክ ከውጤታማነት ባሻገር በወጣቶች ላይ ያለው እምነት ፣ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ውብ እንቅስቃሴው እንዲሁም በርካታ ደጋፊዎቹን ካጣ 15 አመታት አልፈውታል፡፡ ባለፉት ተከታታይ አመታት ደግሞ ላለመውረድ የሚንገዳገድ ክለብ ሆኗል፡፡
በ2009 የውድድር አመት ከአርባምንጭ ከተማ በመቀጠል ብዙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ እንደ ኢትዮ ኤሌትሪክ የለም፡፡ በ30 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች 6 ሲያሸንፍ 9 ተሸንፎ ፣ በ15 ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቆ ፣ 23 ጎል ሲያስቆጠር 24 ጎል ተቆጥሮበት በ33 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወቃል።
ለዘንድሮ የውድድር አመት በምክትል አሰልጣኝ ኤርሚያስ ተፈሪ እየተመራ ከነሐሴ 20 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ታደሰ እንጆሪ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ግቢ ሜዳ ልምምዱን እያደረገ ይገኛል።
ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር ተለያይተው ወደ ሌላ ክለብ ያመሩ ተጨዋቾች አለምነህ ግርማ ፣ በረከት ተሰማ ፣ ዋለልኝ ገብሬ ፣ ብሩክ አየለ ፣ አሸናፊ ሽብሩ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ሙሉአለም ጥላሁን ፣ ፍፁም ገ/ማርያም እና ኢብራሂማ ፎፋና ሲሆኑ የአዲስ ተስፋዬ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ አወት ገ/ሚካኤል እና በኃይሉ ተሻገርን ውል አራዝመዋል፡፡
ክለቡ በርካታ ተጫዋቶች እንደመልቀቁ መጠን በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾትን አስፈርሟል፡፡ ዮሐንስ በዛብህ ( ግብጠባቂ/ ኢትዮዽያ ቡና) ፣ ሞገስ ታደሰ ( ተከላካይ/አዳማ ከተማ) ፣ ግርማ በቀለ ( ተከላካይ/ንግድ ባንክ) ፣ ኄኖክ ካሳሁን ( አማካይ/ ጅማ አባቡና) ፣ ጥላሁን ወልዴ ( አማካይ/ንግድ ባንክ ) ፣ ጫላ ድሪባ ( አጥቂ/ወልድያ) እና ኃይሌ እሸቱ (አጥቂ/አአ ከተማ) ለክለቡ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
በክለቡ የሙከራ ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት አልሳን ካሉሺያ ( አጥቂ/ ጋና ) እና ለብሪ ጋሪኮን ኦዴር ( አጥቂ/ኮትዲቯር ) በሙከራ ወቅት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመነሳት እንደሚፈርሙ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ታዳጊዎችን ወደ ዋናው ቡድን አሳድጎ በመጠቀም ቅድሚያ ስፍራ ከሚሰጣቸው ክለቦች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ኢትዮ ኤሌትሪክ እንደከዚህ ቀደሙ በታዳጊዎች ላይ ያለው እምነት እየቀዘቀዘ በግዢ ተጨዋቾችን በብዛት እያመጣ መወዳደር ከጀመረ ሰንበት ብሏል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ወደ ዋናው ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾችም እምብዛም የመሰለፍ እድል አላገኙም፡፡ ዘንድሮም ክለቡ ከተስፋ ቡድኑ ስድስት ታዳጊዎችን ለሙከራ ወደ ዋናው ቡድን አምጥቶ እያሰራ ይገኛል። እነሱም እሸቴ ተሾመ (ግብ ጠባቂ ) ፣ ጌታሰጠኝ ሸዋ ፣ ዮሀንስ ተስፋዬ ፣ ወልደ አማኑኤል ጌቱ ፣ ካሊድ መሀመድ እና አማኑኤል ጋዲሳ ናቸው ።
የቡድኑ ዝግጅት አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት ም/አሰልጣኝ ኤርምያስ ተፈሪ ዝግጅታቸውን ከነሐሴ 20 ጀምረው በቀን ሁለት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ ገልፀው የክለቡን ውጤታማነት ለመመለስ ጠንክረው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“ያለፉትን ሁለት አመታት በተለይ ላለመውረድ መጫወታችን ድክመት ነው። ከዚህ ድክመታችን በመነሳት አስቀድመን የምንፈልጋቸውን ተጨዋቾች አስፈርመናል፡፡ ጥሩ ዝግጅትም እያደረግን ነው፡፡ ይህ ክለብ ታሪካዊ ክለብ ነው ለዚህ የሚመጥን ውጤት በዘንድሮ ውድድር አመት ለማስመዝገብ እንሰራለን፡፡ ” ያሉት አሰልጣኝ ኤርሚያስ የቡድን ስብጥራቸው በተለይም በአማካይ ክፍል ላይ ያለው መሳሳት ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
” እርግጥ ነው በአጥቂ እና በተከላካይ ስፍራ ላይ ጥሩ አማራጭ አለን፡፡ አማካይ ስፍራ ላይ ግን ክፍተት አለብን፡፡ ባሉት ቀናት በፍጥነት የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾቻንን አማራጭ ለማስፋት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማምጣት እንቀሳቀሳለን” ብለዋል።
የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉትን ጨዋታ ተከትሎ ከጨዋታው በፊት ሀዋሳ ከተማዎች የጨዋታ ውጤት አላግባብ ማስቀየር ሊፈፀም ሲል ደርሼበታለው በማለት በተጫዋች ኤፍሬም ዘካርያስ ላይ የሁለት አመት ቅጣት መቅጣቱን ተከትሎ የኢትዮዽየ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን ትኩረት በመስጠት አጣሪ ኮሚቴ በመመደብ የመጀመርያ ሪፖርቱን ለገዜጠኞች ይፋ ባደረገበት ወቅት በሀዋሳ ከተማ እና በኢትዮ ኤሌትሪክ ጨዋታ በፊት ውጤት ለማስቀየር ሙከራ ተፈፅሟል በማለት ወደ ህግ መምራቱ የሚታወቅ ሲሆን ጉዳዩም እስካሁን ድረስ ምንም ውሳኔ ሳያገኝ ቀርቷል ።
ኢትዮ ኤሌትሪክ የቡድኑን ወቅታዊ አቋም ለመፈተሽ መስከረም 20 ይደረጋል ተብሎ ቀን በተቆረጠለት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፍ ክለቡ አረጋግጧል ።