የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት የስፖርት ዘርፎች ያዘጋጀው የሽልማት ስነስርዓት ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ከ400 በላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፊት ለአሸናፊዎቹ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጨዋች፣ በምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች፣ በምርጥ ወንድ አትሌት እና በምርጥ ሴት አትሌት ዘርፍ ተቋሙ እጩዎችን ቀደም ብሎ በባለሙያዎች እና በእግር ኳስ ቤተሰቡ ምርጫ መሰረት ይፋ ያደረገ ሲሆን በአይነቱ ለየት ያለ እና ስፖርተኞቻችንን ለማበረታታት ታስቦ ዝግጅቱ እንደተዘጋጀ ከዚህ ቀደም በጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
በእግር ኳስ ተጨዋቾች ዘርፍ ለእጩነት የተመረጡት ተጨዋቾች በውድድር ዘመኑ በሃገር ውስጥ ሊግ ማለትም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ በከፍተኛ ሊግ ወይም በአንደኛ ሊግ እና በሌሎች ሀገሮች ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ጨምሮ በብሄራዊ ቡድን ባሳዩት ብቃት እንደተመረጡ ተገልጿል፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነትም አርአያ የሆኑ ተጨዋቾችን ለማካተት ጥረት እንደተደረገ በመድረኩ ተገልጻል፡፡
በሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ዘርፍ ለመጨረሻ የደረሱት እጩዎች ሰናይት ቦጋለ፣ ሎዛ አበራ እና ወይንሸት ጸጋዬ ሲሆኑ የደደቢቷ የፊት መስመር ተጫዋች ሎዛ አበራ በአንደኝነት በማሸነፍ ከኢንስትራክተር በለጥሽ ገብረማርያም እጅ የዋንጫ እና የ75 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማቷን በተወካይዋ በኩል ተረክባለች።
በወንድ እግር ኳስ ተጨዋቾች ዘርፍ ደግሞ ጌታነህ ከበደ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና አስቻለው ታመነ የመጨረሻው የተጨዋቾች ዝርዘር ውስጥ የገቡ ሲሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የተከላካይ መስመር ተጨዋች አስቻለው ታመነ በበላይነት በማሸነፍ በተመሳሳይ የዋንጫ እና የ75 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማቱን ከቀድሞ የኢትየጵያ ብሄራዊ ቡድን ኮከብ ንጉሴ ገብሬ እጅ ተቀብሏል።
በአትሌቲክስ በምርጥ ወንድ አትሌት ዘርፍ ሙክታር ኢድሪስ በምርጥ ሴት አትሌት አልማዝ አያና አሸናፊ ሲሆኑ እንደ እግር ኳስ ተጨዋቾቹ ሁሉ የዋንጫ እና የ75 ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።