​ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፈው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመቐለ ከተማ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል ።

የወልዋሎ እግርኳስ ክለብ የምስረታው ታሪክ ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ ቢሆንም በተደጋጋሚ የመፍረስና እንደአዲስ የመቋቋም ሒደቶችን እያለፈ ከ2004 ጀምሮ በሀገሪቱ ዝቅተኛ የሊግ እርከኖች ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ በ2009 በከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ ውድድሩ ከተጀመረ አንስቶ የአንደኝነቱን ደረጃ ሳይለቅ ከበርካታ ደጋፊዎቹ ጋር ታግዞ አንደኛ በመሆን የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን አረጋግጧል።

በ2010 የውድድር አመት ለፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ  ይረዳው ዘንድ ቡድኑን በአዲስ መልክ እያደራጀ ይገኛል፡፡ በቡድኑ የአምና ስብስብ ውስጥ ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል አብዱስላም አማን ፣ ቴዎድሮስ መንገሻ ፣ ስኡድ ኑር እና ግርማ ፀጋዬን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ሲለቁ በምትኩ 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡


ዋልዋሎ አዲስ ያስፈረማቸው ተጨዋቾች እንየው ካሳሁን ( ተከላካይ/አአ ከተማ) ፣ ሮቤል ግርማ ( ተከላካይ/ንግድ ባንክ) ፣ በረከት ተሰማ ( ተከላካይ/ኢትዮ ኤሌትሪክ) ፣ ተስፋዬ ዲባባ ( ተከላካይ/ድሬዳዋ ከተማ) ፣ ብሩክ አየለ ( አማካይ/ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣  ወግደረስ ታዬ ( አማካይ/ደደቢት) ፣ ቢንያም አየለ ( አጥቂ/አዳማ ከተማ) ፣ ሙሉአለም ጥላሁን ( አጥቂ/ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ እዮብ ወልደማርያም( አጥቂ/ አማራ ውሀ ስራ ) ናቸው።

ቢጫ ለባሾቹ ሦስት የጋና ዜግነት ያላቸው አብዱራህማን ፉሱኒ ፣ ፍሬዲክ ቦቴንግ ፣ አቲያ ሳሙኤል የተባሉ ተጫዋቾችን እየሞከሩ ሲሆን ሁለቱ የተሳካ የሙከራ ጊዜ አድርገው ከቡድኑ ጋር ሊቆዩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ክለቡ በቀጣይ ቀናት ማስፈረሙ ሲረጋገጥም የተጫዋቾቹን ፕሮፋይል ይዘን የምንቀርብ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ወልዋሎ በአሰልጣኝ ብርሃኔ እየተመራ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በመቐለ ከተማ በአዲሱ ስታድየም ሁለተኛ ሜዳ ዝግጅቱን በሚገባ እያከናወነ ይገኛል።

አሰልጣኝ ብርሃኔ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ ስለ ዝግጅታቸው ተናግረዋል፡፡ “የተወሰኑ ቀናት በአዲግራት ልምምዶች ከሰራን በኋላ የሜዳ ችግር ቢያጋጥመንም የመቐለ ወጣቶችና ስፖርት ሚንስቴር ባዘጋጀልን ምቹ ሜዳ ላይ ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ እያደረግን እንገኛለን” በማለት ገልፀዋል። 


ቡድኑ ለሊጉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ቀደም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዳደጉት ሁሉ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ቢገመትም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማሰባሰቡ እንደማይቸገር አሰልጣኝ ብርሀኔ ገልጸዋል፡፡ ” ወልዋሎ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስብስብ ነው፡፡ በሊጉ የሚያሰጋው ነገር የለም፡፡ እንደሚታወቀው በአዳማ ከተማ እና በሌሎችም ክለቦች ሰርቻለው፡፡ ፕሪምየር ሊጉን እናቀዋለን፡፡ ስለዚህ እኛን አያሰጋንም፡፡ አዲስ ያመጣናቸው ልጆችም ቡድኑን በሚገባ የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ በዝግጅት ወቅትም በአካል ብቃት ፣ በቅንጅታቸውም ጥሩ ናቸው። በዘንድሮ የውድድር አመትም በፕሪምየር ሊጉ ወልዋሎን ኃይለኛ ተወዳዳሪ ፣ ጠንካራ ቡድን እና ወጥ አቋም ያለው ቡድን ይዘን እንቀርባለን” ብለዋል ።

ወልዋሎ የቡድኑን አቋም ለመፈተሽ መስከረም 13 በሚጀምረው የደቡብ ካስት ካፕ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን አሰልጣኝ ብርሃኔ ማረጋገጫ ሰተውናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *