​የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የሚጀመርበት ቀን ተራዘመ

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚያዘጋጀው የ2010 የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ውድድር የሚያካሄድበትን ቀን ማራዘሙን አስታወቀ፡፡

የዘንድሮ የሲቲ ካፕ ውድድር ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 4 ለማድረግ ታስቦ እንደነበረ ከዚህ ቀደም መገለፁ የሚታወስ ሲሆን ፌደሬሽኑ በዝናብ ምክንያት የአዲስ አበባ ስታዲየም ሜዳ ምቹ አለመሆኑ እና ለጨዋታ ብቁ አለመሆኑን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በመግለፅ ውድድሩ የሚደረግበትን ጊዜ ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 11 ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

ዛሬ ረፋድ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ በለጠ ዘውዴ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ጨምሮ ሌሎች የፌደሬሽኑ አባላት በተገኙበት የአዲስ አበባ ስታዲየምን ወቅታዊ ሁኔታ መመልከታቸውን የገለፁ ሲሆን የሁለቱም የፌደሬሽን አካላት ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑን በመተማመን የውድድሩን ጊዜ እንዲገፋ በቃል መስማማታቸውን አቶ በለጠ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ሁሉም ክለቦች በይፋ ተለይተው ያልታወቁ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ ሁሉም በሊጉ ላይ የሚወዳደሩት የአዲስ አበባ ክለቦች እንደሚሳተፉ ግን ተነግሯል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምን አልባት በዚህኛው ውድድር ላይ ላይሳተፍ እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስረፃሚ አባል የሆኑት አቶ በለጠ ዘውዴ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ክለቡ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከሌሎች ክለቦች ጋር ለማድረግ መርሃ ግብር ማውጣቱን በመግለፁ ነው ብለዋል፡፡ ክለቡ በውድድሩ ላይ እንዲሳተፍ  ድርድሮች እየተደረጉ መሆኑን የገለፁት አቶ በለጠ ምን አልባት ከአቅም በላይ የሚፈጠር ችግር ካጋጠመ ቡድኑ በወጣት ቡድኑ እንዲሳተፍ ሊደረግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የክልል ተጋባዥ ክለቦችን በተመለከተ ጥያቄ ከቀረበላቸው ክለቦች ውስጥ አዳማ ከተማ ብቻ ምላሽ መስጠቱ ሲገለፅ ሌሎች ተጋባዥ ክለቦች መልስ እየተጠበቀ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *