የኢትዮጵያ ዋንጫ ሰኔ 28 ይፈፀማል

የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሰኔ 24 ቀን 2006 አ.ም. እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ዘንድሮ በ14 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል ብቻ የተደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር አንደኛ ዙር ህዳር መጨረሻ ሁለተኛው ደግሞ ጥር ወር ላይ የተደረጉ ሲሆን የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ በመጋቢት ወር ተካሂደዋል፡፡

የግማሽ ፍፃሜዎቹ ጨዋታዎች ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2006 ሲካሄዱ በ9 ሰአት ደደቢት ከመከላከያ ይፋለማሉ፡፡ ደደቢት እዚህ ለመድረስ የተጫወተው ጨዋታ ብዛት አንድ ብቻ ሲሆን በሩብ ፍፃሜው አርባምንጭ ከነማን አሸንፎ የመጣው ንግድ ባንክን አሸንፎ ለግማሽ ፍፃሜ በቅቷል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን መከላከያ በበኩሉ በመጀመርያው ዙር ወላይታ ድቻን ፣ በሩብ ፍፃሜው ደግሞ ሐረር ሲቲን አሸንፎ ለግማሽ ፍፃሜ በቅቷል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙገርን አሸንፎ ወደ ፍፃሜው እንደሚያልፍ ገምተው ወደ ሜዳ ከገቡ ፍልሚያቸው የፍፃሜ ያህል ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፃሜውን ከተቀላቀለ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ የደደቢት እና የመከላከያ አሸናፊ ፍጻሜ በመድረሱ ብቻ የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳትፎን ያረጋግጣል፡፡

ከሁለቱ ጨዋታ በመቀጠል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሙገር ሲሚንቶ ይፋለማሉ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች አምና በተመሳሳይ በጥሎ ማለፉ ግማሽ ፍፃሜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸንፎ ፍፃሜውን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ደደቢት ሁሉ እዚህ ለመድረስ 1 ጨዋታ ብቻ ያደረገ ሲሆን በኡመድ ኡኩሪ የመጨረሻ ሰአት ግብ ሲዳማ ቡናን አሸንፎ ለግማሽ ፍፃሜ በቅቷል፡፡ ሙገር በበኩሉ ሀዋሳ ከነማን 2-1 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 አሸንፎ ለግማሽ ፍጻሜው በቅቷል፡፡

የግማሽ ፍፃሜው አሸፊዎቸ እሁድ ሰኔ 28 ቀን 2006 አም ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ሲያልፉ የውድድሩ አሸናፊ አልያም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ፍፃሜ የሚቀርብ ክለብ ለ2015 የአፍሪካ ኮንፌድሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ ማለፉን ማለፉን ያረጋግጣል፡፡

ያጋሩ