አርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ሜዳ በቀን ሁለት ጊዜ ዝግጅቱን እየሰራ ይገኛል።
በ2004 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ ወዲህ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የቆየው አርባምንጭ በ2009 የውድድር ዘመን በውጤት ቀውስ ውስጥ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ዻውሎስ ጸጋዬን እና የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጣሳውን ማሰናበቱ የሚታወቅ ነው።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 30 ጨዋታዎች 6 ሲያሸንፍ 8 ተሸንፎ በ16 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 25 ጎል አስቆጥሮ 32 ጎል ተቆጥሮበት በ34 ነጥብ 12ኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ቡድኑ የመጨረሻውን ሳምንት ጨዋታ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በአቻ ውጤት ጨዋታን በማጠናቀቁ በሊጉ ሊሰነብት ቻለ እንጂ ላለመውረድ ሲንገዳገድ የነበረ ቡድን ነበር። በርካታ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ቀዳሚው ክለብ ነበር፡፡ ከዚህ ድክመቱ በመነሳት የተለያዩ የአሰራር ፣ የአደረጃጀት እና የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ ለዘንድሮ ውድድር አመት እየተዘጋጀ ይገኛል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያምን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው አርባምንጭ ከተማ ሦስት ተጨዋቾችን ከሀገር ውስጥ ሲያስፈርም በክለቡ ታሪክ የመጀመርያ የሆኑ ሁለት ተጨዋቾችን ደግሞ ከውጭ ማስፈረም ችሏል።
አርባምንጭ ከተማ ማልያ ጋር በዘንድሮ አመት የማንመለከታቸው ተጨዋቾች ታሪኩ ጎጀሌ ፣ አመለ ሚሊኪያስ እና ታደለ መንገሻ ሲሆኑ ቡድኑ በዘንድሮ አመት ለማገልገል ፊርማቸውን ያኖሩ ተጨዋቾች ደግሞ ሲሳይ ባንጫ ( ግብጠባቂ/ጅማ አባቡና) ፣ ታዲዮስ ወልዴ ( አማካይ/ንግድ ባንክ) ፣ ዮናታን ከበደ ( አጥቂ/ ሀዋሳ ከተማ) ናቸው።
እንደ ሌላው የደቡብ ክለብ ወላይታ ድቻ ሁሉ የአርባምንጭ ከተማ ማልያን ለመጀመርያ ጊዜ የሚለብሱ ሁለት የውጭ ተጨዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡ እነሱም ላኪ ሳኒ ( አጥቂ/ናይጄርያ) እና ሰይዶ ባንሴ ( አጥቂ/ጋና ) ናቸው፡፡ አማዙ አሌክስ ( ተከላካይ/ከጋና) ከቡድኑ ጋር የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ ሲገኝ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቶ አሰልጣኞቹን ካሳመነ የሚፈርም ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ይህ የማይሳካ ከሆነ ሌላ የመሀል ተከላካይ ክለቡ ሊያመጣ እንደሚችል ሰምተናል።
አርባምንጭ ከተማ ከ20 እና ከ17 አመት በታች በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፍ ቡድን ባይኖረውም ታዳጊዎችን ከአካባቢው በመመልመል በሚያሳድግበት ባህሉ ቀጥሎ አሁን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው እየሰሩ የሚገኙ አራት ተጨዋቾችን ተመልክተናል። እነሱም ታሪኩ ኰርቶ (አምና በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል) ፣ ዱሬ አንሎ ፣ ብሩክ ዋኵ እና እስራኤል ሻጎሌ ናቸው ።
አዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ለስልጠና ወደ ሞሮኮ ማቅናታቸውን ተከትሎ ያለፉትን አስራ አምስት ቀናት በምክትል አሰልጣኙ በረከት ደሙ መሪነት በአርባምንጭ ዩንቨሪሲቲ ሜዳ በቀን ሁለት ልመምዱን እየሰራ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ አማካዩ ምንተስኖት አበራ በጉዳት ፣ አዲሱ ፈራሚ ሰይዱ ባንሴ የወረቀት ጉዳይ ለመጨረስ ወደ አዲስ አበባ በመሄዱ ምክንያት ያልተገኙ ሲሆን ፀጋዬ አበራ እና እንዳለ ከበደ በመጠነኛ ጉዳት ሙሉ ልምምድ ያልሰሩ ተጨዋች ናቸው፡፡ የተቀሩት 25 ተጨዋቾች ግን ልምምዳቸውን ሲሰሩ ተመልክተናል።
ይህንን ዘገባ ለማጠናከር አርባምንጭ ከተማ በተገኘንበት ወቅት ከቡድኑ ጋር ያልነበሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም እና ሰይዶ ባንሴ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ሰምተናል።
ምክትል አሰልጣኙ በረከት ደሙ ከሶከር ኢትዮዽያ ባደረጉት ቆይታ ያለፈውን አመት መጥፎ ውጤት ለመቀየር በጠንካራ ዝግጅት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም የቡድኑ ችግር የነበረው ወጥ አቋም አለማሳየትን ለመቅረፍ እየሰሩ እነንደሎነ ገልጸዋል፡፡
” ብዙ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀናል፡፡ ያም የሆነው ወጥ የሆነ አቋም ካለማሳየት እና ደካማ የሆነው የአጥቂ መስመር አጨዋወታችን ብዙ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ስንችል በአቻ ውጤት እንድንጨርስ አድርጎናል፡፡ ያንን ክፍተታችን ለማሻሻል አዳዲስ ተጨዋቾችን አስፈርመናል፡፡ እርግጥ ነው በዝውውርር ገበያው ዘግይተን እንደመግባታችን ያሰብናቸውን ልጆች አላገኘንም፡፡ ያም ሆኖ ቦታውን በትክክል ይሸፍኑልናል ብለን ያሰብናቸውን ልጆች እያስፈርምናል፡፡ የባለፈው ድክመታችን እንዳይደገም ጠንክረን እንሰራለን፡፡ እርግጠኛ ነኝ በሊጉ ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ቡድኖች አንዱ እንሆናለን፡፡ ” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከአካባቢው የሚገኙ ተጫዋቾች ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርግ የቆየው አርባምንጭ በዚህ ክረምት አሰራሩን በመቀየር የውጪ ተጫዋቾችን ጭምር ማምጣት ቸሏል፡፡ ክለቡም ለውሳኔው በሀገሪቱ ያለው የአጥቂ ችግር አስተዋጽኦ እንዳደረገ አሰልጣኝ በረከት ገለጸዋል፡፡
” አርባምንጭ በርካታ ተጨዋቾችን የሚያፈራ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ባለፈው አመት ውጤታችን ያየን እንደሆነ የማጥቃት ችግሮች ነበሩብን፡፡ ይሄንን ችግር ቀርፈን ካሉት ቡድኖች ጋር ተፎካካሪ መሆን ስላሰብን ብቻ የውጭ ተጨዋቾችን አምጥተናል። ከዛ በተረፈ ላሉት ታዳጊዎች እና ጥቂት አመት ከክለቡ ጋር ለቆዩ ተጨዋቾች ልምድ ይሰጣሉ በሚል አዳዲስ ተጫዋቾች አምጥተናል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮዽያ ውስጥ ብዙ ጠንካራ አጥቂዎች በብዛት አይገኙም፡፡ ለዛ ነው የውጭ ተጨዋቾችን ያመጣነው እንጂ በሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ሳናምን ቀርተን አይደለም፡፡ የምንፈልገውን ልምድ ካገኘን በኋላ ፊታችንን ወደ ሀገር ውስጥ ተጨዋቾቾች እናዞራለን” ብለዋል፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከሊጉ መጀመር በፊት በደቡብ ካስትል ዋንጫ ላይ ይሳተፋል፡፡ ክለቡ ባለፈው አመት በዚህ ውድድር ላይ ለፍጻሜ ደርሶ በሲዳማ ቡና መሸነፉ ይታወሳል፡፡