ፓሽን ስፖርት አካዳሚ የሚሳተፍበት አለም አቀፍ ውድድር ነገ ይጀመራል

 

በቀድሞ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የተቋቋመውና በራሊ ፉትቦል ዴቨሎፕመንት ስር የሚገኘው ፓሽን ስፖርት አካዳሚ ከ10 አመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን በመያዝ ማሰልጠን ከጀመረ አመት አልፎታል፡፡ ቡድኑ ከሌሎች የሃገራችን የታዳጊ ቡድኖች በተለየ በውጭ ሃገራት በሚዘጋጁ የታዳጊዎች ውድድር ላይ በመካፈል ለታዳጊዎች ከወዲሁ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ልምድ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡

አካዳሚው አምና በቺካጎ በተደረገው ውድድር የተሳተፈ ሲሆን 3 ጨዋታዎችን አድርጎ መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ነገ በሚጀመረውና በሁለቱም ፆታዎች ከ11 አመት እስከ 18 አመት በሚገኙ የእድሜ እርከኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቡድኖችን ባሰባሰበው የጎቲያ ውድድር ላይ በ14 አመት በታች ቡድኑ ለመሳተፍ ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ ውድድር ከአዲስ አበባ በ5900 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በስዊድኗ ጉተንበርግ ከተማ ሲካሄድ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች የሆኑትን ፒኤስጂ ፣ ኒውካስል ዩናይትድ እና አያክስ አምስተርዳምን ጨምሮ 1700 ቡድኖች ፣ ከ50ሺህ በላይ ታዳጊዎች እና አጠቃላይ የልኡካን ቡድን ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከ100 በሚልቁ ሜዳዎች 4000 ጨዋታዎች የሚካሄድበት እና 500 ዳኞች በሚሳተፉበት ውድድርም በነገው እለት በኡሌቪ ስታድየም የመክፈቻው ስነስርአት ይካሄዳል፡፡

10471087_941343292576371_6616336667248698101_n

ይህ ውድድር በ1970ዎቹ አጋማሽ ከ5 ሃገራት በተውጣጡ 275 ቡድኖች የተጀመረ ሲሆን በ2014 የተሳታፊዎች ቁጥር 73 ሃገራት እና 1670 ቡድኖች ላይ መድረስ ችሏል፡፡ በአእምሮ እድገት ዝግመት ለተጠቁ ታዳጊዎች የተዘጋጀና በቀድሞው የስዊድን ብሄራዊ ቡድን እና ኦሎምፒክ ሊዮን ኮከብ ኪም ካልስትሮም ስፖንሰር የሚደረገው ውድድርም የዚህ ፌስቲቫል አንዱ አካል ነው፡፡

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ክፍያ 100 ዩሮ ሲሆን የአካዳሚው ባለቤቶች ከወራት በፊት ከኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ጋር ባደረጉት ቆይታ ለኢንተርናሽናል ውድድሮች ወደ ውጪ ሃገራት ሲጓዙ የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎችን የሚሸፍኑት የተጫዋቾቹ ቤተሰቦች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

 

ያጋሩ