ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ የቡርኪና ፋሶ እና ሁለት የጋና ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል፡፡
የአምናውን የውድድር ዘመን በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፈው ፕሪንስ ሰቨሪን ዋንጎ ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ ፕሪንስ በአአ ከተማ ዋንጫ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሰለፈ በኋላ በሊጉ ሳይመዘገብ መቅረቱን ተከትሎ የመጀመርያውን ዙር ሳይጫወት ቆይቶ በሁለተኛው ዙር በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡
ጋናዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፍሬዲክ ቦአቴንግ ሌላው ለክለቡ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ ቦአቴንግ ከሌሎች ጋናዊያን ጋር በመሆን በወልዋሎ የሙከራ ጊዜ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ባሳየው አጥጋቢ እንቅስቃሴ ለክለቡ ፈርሟል፡፡ ተጫዋቹ በሀገሩ ክለቦች ኢቡሱዋ ዱዋርፍ እና ኢንተር አላይንስ ተጫውቷል፡፡
ከቦአቴንግ ጋር የሙከራ ጊዜ ለማሳለፍ የመጣው አብዱልራህማን ፉሴይኒ ቋሚ ኮንትራት ፈርሟል፡፡ ጋናዊው አማካይ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ለሀገሩ የአንደኛ ዲቪዝዮን ክለብ ስቲድፋስት ተጫውቷል፡፡
ወልዋሎ ከሶስቱ የውጪ ዜጎች በተጨማሪ ከ10 በላይ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ አስፈርሟል፡፡