የካፍ ዋንጫ እና የካፍ ክለብ ዋንጫ ከተዋህዱ በኃላ ለ14ኛ ግዜ በሚካሄደው የቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦችን ለመለየት የሚደረጉ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ሴፋክ ላይ በሚደረግ ጨዋታ ይጀመራል፡፡
ከሳምንት በፊት ራባት ላይ ፉስ ራባት ሴፋክሲየንን 1-0 የረታ ሲሆን ይህንን የጠበበ መሪነት ይዞ ወደ ቱኒዚያ አምርቷል፡፡ ሴፋክሲየን ፋስ ራባትን በሚያስተናግድበት የሰሜን አፍሪካ ደርቢ ጨዋታ የሚጠበቅ ሲሆን ፋስ ራባት በአዲሱ የውድድር ዘመን መሻሻልን በሞሮኮ ቦቶላ ሊግ በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ የአምናው ቻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካን 3-1 የረታ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ሴፋክሲየንን በሜዳው 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በቱኒዚያ ሊግ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሃያሎቹን ኤስፔራንስ፣ ኤትዋል ደ ሳህል እና ክለብ አፍሪካ የበላይነት መስበር ያልቻለው ሴፋክሲየን በየአመቱ በሚያፈልቃቸው ጥሩ ጥሩ ታዳጊዎች ታግዞ የአፍሪካ የክለቦች እግርኳስ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ነው፡፡ ሴፋክሲየን በሜዳው ጠንካራ ሪከርድ ያለው ሲሆን ለመጨረሻ ግዜ በሜዳው ያደረገውን የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታ የአልጄሪያው ኤምሲ አልጀር ላይ በርካታ ግብ በማስቆጠር ነው የጨረሰው፡፡ በሁለቱ ክለቦች መካከል በተደረገው ጨዋታ የተመዘገበው ውጤት ጠባብ መሆኑን ተከትሎ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡ ሴፋክሲየን በ2013 እንዲሁም ፉስ ራባት በ20 የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ከሆኑ በኃላ ዋንጫው ማንሳት አልቻሉም፡፡
ጨዋታው የሚመራው ዴቪስ ኦምዌኖ ነው፡፡ ኬንያዊው አርቢትር ዴቪስ ከሳምንት በፊት የበርካታ ሚዲያዎች መነጋገሪ ሆኖ ነበር፡፡ የመሃል ዳኛው ቱኒዚያ ከሊቢያ በህዳር 2016 ያደረጉትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከመራ በኃላ ሶስት ወራት ታግዶ የነበረ ሲሆን የሊቢያ እግርኳስ ፌድሬሽን ዴቪስ ቱኒዚያዊ ባለቤት ስላለችው ጨዋታውን የመምራት ብቃት አልነበረውም በሚል ለፊፋ ጨዋታው እንዲደገምለት ጠይቋል፡፡
የዛሬ ጨዋታ
19፡00 – ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ስታደ ጣሂብ ማሂሪ)
የቅዳሜ ጨዋታ
15፡00 – ዜስኮ ዩናይትድ ከ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም)
የእሁድ ጨዋታዎች
15፡30 – ቲፒ ማዜምቤ ከ አል ሂላል ኦብዬድ (ስታደ ቲፒ ማዜምቤ)
19፡00 – ክለብ አፍሪካ ከ ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)