የደቡብ ካስትል ዋንጫ ዛሬ በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም በተደረጉ ሁለት የምድብ ሀ ጨዋታዎች ሲጀመር ፋሲል ከተማ እና ወላይታ ድቻ ውድድራቸውን በድል ጀምረዋል፡፡
ሀዋሳ ከተማ 1-3 ፋሲል ከተማ
የውድድሩ የመጀመርያ ጨዋታን በክብር እንግድነት ተገኝተው ያስጀመሩት አቶ ታመነ ተሰማ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ኃላፊ እና አቶ ደመላሽ ይትባረክ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ከተያዘለት ጊዜ ከ20 ደቂቃ በላይ ዘግይቶ የተጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከተማ በማጥቃቱ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ ሲችል ሀዋሳ ከተማ በዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ከሚፈጠሩ እድሎች በቀር ተዳክመው ታይተዋል፡፡
በ12ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙገርዋ ያመቻቸለትን ኳስ ኤርሚያስ ኃይሉ አስቆጥሮ ፋሲሎችን ቀዳሚ አድርጎል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲሎቸ ጫና ፈጥረው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በራምኬል ሎክ ፣ ፊሊፕ ዳውዝ እና ኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ይሁንና በመልሶ ማጥቃት ሀዋሳ ከተማዎች በፈጠሩት ጫና በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አይናለም ኃይሉ በዳዊት ፍቃዱ ላይ በሰራው ጥፋት በ16ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን አስቆጥሮ ሀዋሳን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ከዕረፍት መልስ ፋሲል ከተማዎች የጨዋታ የበላይነት ማሳየት ሲችሉ ሀዋሳ በ46ኛው ደቂቃ ላይም በፋሲል በኩል ጥሩ የነበረው ያስር ሙገርዋ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ፊሊፕ ዳውዝ ተጠቅሞ ለአዲሱ ክለቡ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ናየጄርያዊው አጥቂ በ55ኛው ደቂቃ ከአምሳሉ ጥላሁን የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የክለቡን መሪነት ወደ 3-1 ማሳደግ ችሏል፡፡
በጨዋታው ላይ አንጋፋው ሙሉአለም ረጋሳ የመጀመርያ አሰላለፍ ውሰጥ ተካቶ የተጫወተ ሲሆን ተቀይሮ እስከ ወጣበት 67ኛው ደቂቃ ድረስ ባደረገው እንቅስቃሴም ከተመልካቹ አድናቆት ተችሮታል፡፡
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፋሲሎች በፊሊፕ ዳውዝ እና ያሬድ ባዬ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ የሚሆኑ እድሎችን ሲያመክኑ በሀዋሳ በኩል ሳዲቅ ሴቾ እና ዳዊት ፍቃዱ በርካታ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ክለቡን ሳይታደጉ ቀርተዋል፡፡ ፋሲል ከተማም 3-1 በሆነ ውጤት አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡ በፋሲል ከተማ በኩል አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ያስር ሙገርዋ በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር ፤ ተክለማርያም ሻንቆ በሀዋሳ ከተማ በኩል በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማምከን የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪዎች ነበሩ፡፡
ወላይታ ድቻ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና
ቀጥሎ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ድጋፍ የታጀበበት ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ከፍለ ጊዜ ኳስን መስርቶ በመጫወት ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ የነበረ ቢሆንም ጠንካራ የነበረው የወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመርን መስበር ተስኖት ታይቷል፡፡
በ44ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከማዕዘን ምት ያሻገራትን ኳስ ሀዲያ ሆሳዕናን ለቆ ድቻን በክረምቱ የተቀላቀለው እርቅይሁን ተስፋዬ በግንባሩ በመግጨት የድቻን ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ አስቆጥሯል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ድንቅ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ86ኛው ደቂቃ ላይ በተቃራኒው የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ቶማስ ስምረቱ በፀጋዬ ብርሀኑ ላይ በሰራው ጥፋት ከኢትዮጵያ ቡና በኩል በቀጥታ ቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡
የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ በተለይም ከ72ኛው ደቂቃ ጀምሮ ጨለማ የነበረ ቢሆንም በሰአቱ የስታድየሙ መብራት አለመብራቱ ለጨዋታ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡