​ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ ሱፐርስፖርት እና ፉስ ራባት ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

በቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ፉስ ራባት ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆኗቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ ታግዞ ዜስኮ ዩናትድን ከውድድር ውጪ ሲያደርግ ፉስ ራባት ሴፋክሲየንን በመለያ ምት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ሴፋክሲየን 1-0 ፉስ ራባት (ፉስ ራባት በመለያ ምት 5-4 አሸንፏል)

የቱኒዚያው ሴፋክሲየን በፉስ ራባት ተሸንፎ ከኮንፌድሬሽን ዋንጫው ውጪ ሆኗል፡፡ ሴፋክሲየን በስታደ ጣሂር ማሂሪ የተደረገውን ጨዋታ 1-0 ቢያሸንፍም በመለያ ምት 5-4 ተሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሳያልፍ ቀርቷል፡፡ እንደተጠበቀው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከባድ ፉክክርን ያስተናገደ ሲሆን አጀማመራቸው መልካም የነበረው ሴፋክሲየኖች በካሪም አዎዲ የ23ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ጨዋታው መሪ መሆን ሲችሉ ፉስ ራባቶች የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አቻ መሆን የሚችሉበትን እድል አምክነዋል፡፡ በሁለተኛው 45 ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ያልተሳካ ጥረት ሲያደርጉ በ90ኛው ደቂቃ ሰዓድ አይት ልኮርሳ ከፉስ ራባት በኩል በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ አላፊውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ፉስ ራባት 5-4 አሸንፏል፡፡ ካሪም አዎዲ በጨዋታ ያስቆጠረውን የፍፁም ቅጣት ምት በመለያ ምቱን መድገም ተስኖት ሴፋክሲየን ከውድድር ውጪ ለመሆን ተገዷል፡፡ ፉስ ራባት በ2010 ሴፋክሲየንን አሸንፎ የውድድሩ ቻምፒዮን ከሆነ በኃላ ዋንጫ ማንሳት አልቻለም፡፡

ዜስኮ ዩናይትድ 2-2 ሱፐርስፖርት ዩናይትድ 

ፕሪቶሪያ ላይ ያለግብ አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ዜስኮ ዩናይትድ የተሻለ እድልን ይዞ ወደ ሜዳ ቢገባም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ያልተጠበቀው ክለብ ሁኗል፡፡ ዜስኮ ዩናይትድ ንዶላ ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታ ስድስት የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ማጠናቀቁን ተከትሎ የማሸነፍ ቅድመ ግምቱ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ጆን ቺጋንዱ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ዜስኮን ገና በአራተኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ  ቱሶ ፓላ በ31ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ ቀኝ መስመር አከባቢ መሬት ለመሬት መቶ ባስቆጠረው ግብ ሱፐርስፖርትን አቻ አድርጓል፡፡ ኬንያዊው ኢንተርናሽናል ዴቪድ ኦዌኖ በ50ኛው ደቂቃ ዜስኮን ዳግም መሪ ያደረገች ግብ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ሲያስቆጥር በ92ኛው ፓላ የሱፐርስፖርት ማለፍ ያረጋገጠች ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ግቧ በሱፐርስፖርት ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ኤሪክ ቲንክለር ላይ ከፍተኛ ደስታን ስትፈጥር ዜስኮን ያልተጠበቀ ተሸናፊ አድርጓል፡፡

ቀሪ አላፊ ሁለት ቡድኖች እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚታወቁ ይሆናል፡፡

ውጤቶች 

ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን 1-0 ፋት ዩኒየን ስፖርት (ፉት ራባት በመለያት ምት 5-4 አሸንፏል)

ዜስኮ ዩናይትድ 2-2 ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ባገባ ህግ አልፏል)

የዛሬ ጨዋታዎች

10፡30 – ቲፒ ማዜምቤ ከ አል ሂላል ኦብዬድ (2-1) (ስታደ ቲፒ ማዜምቤ)

3፡00 – ክለብ አፍሪካ ከ ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (0-1) (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *