የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከተፈፀመ በኋላ የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረ መስቀል እና የቦርድ አመራሮች አቶ ንዋይ እና አቶ ዳዊት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ሰፊ ምላሽ አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው አሰናድተን አቅርበነዋል።
ክለቡ ይፋ ስላደረገው ወደ አክሲዮን ሽግግር እቅድ
አቶ አብነት፡ ይህ መነሻ ሀሳብ ነው ፤ ገና ውሳኔ አልተሰጠበትም፡፡ ይህም የአክስዮን ድርሻ ብዙዎችን እንዲያገል አይደለም የምንፈልገው፡፡ ሁሉም የሚታቀፍበትን መንገድ ነው እየፈጠርን ያለነው። ክለቡ በባላሀብት ብቻ ተይዞ የባለሀብቶች ክለብ ብቻ ሆኖ ሌላው ጊዮርጊስን ብሎ ፀሀይ ብርድ የሚቀጠቅጠውን ክለቡን እዚህ ያደረሰውን ህዝብ ትተን እንጓዝ ቢባል እኛም እሺ አንልም። ይህ ጥናት የቀረበው መነሻ ሀሳብ ነው አንድ ሚሊዮን የአክሲዮን መነሻ ሀሳቡ በዝቷል እታች ያለውን ደጋፊ አቅም ያማከለ አይደለም ከተባለ እንዴት አጣጥመን እንደምንሄድ ጥናቱን ካጠኑት ሰዎች ጋር ተነጋግረን በማስተካከል የምንሄድበት ነው የሚሆነው። አንድ ነገር መግለፅ የምፈልገው የአለም እግር ኳስ አደረጃጀት እየተቀየረ ነው የመጣው እኛም ራሳችንን ወደ ዘመኑ አሰራር እየከተትን ካልሄድን የትም አንደርስም፡፡ መቀየር አለበት አለበለዚያ ሌሎች ሀገሮች ከደረሱበት ደረጃ ሳንደርስ እኛም ሆንን ብሔራዊ ቡድን መፎካከር አንችልም ፤ ሀብት ሊኖረን ያስፈልጋል። ስለዚህ በዚህ መሰረት ታይቶ የክለቡን አቅም ልናሳድግ ይገባል። የኢትዮዽያ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች ራሳቸውን ችለው ሀብት የሚያሰባስቡበትን ህግ አሰራራቸውን ከልሰው በማየት አዲስ ማሻሻያ ህግ ቢያስቀምጥ መልካም ነው።
ከሌሎች የአፍሪካ ክለቦች የተወሰዱ ተሞክሮዎች
አቶ አብነት፡ ከአንድም ሁለት ሦስት የአፍሪካ ክለቦች ፕሬዝዳንቶች ጋር አውርተናል ፤ ልምድም እየተለዋወጥን እንገኝለን፡፡ የግብፅ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዩጋንዳ አብዛኞዎቹ ሀገራት በመንግስት ባጀት ነው የሚተዳደሩት፡፡ የተወሰኑት ናቸው የህዝብ ክለቦች ያሉት። ሁሉም ነፃ መሆን ይፈልጋሉ ፤ አፍሪካ ስታድግ ስትበለፅግ በሁሉም ነገር የተሻለ ይሆናል። ክለቦች በራሳቸው የፋይናስ አቅም ሊመሩ ይገባል፡፡ አለበለዝያ ከሌሎች ሀገራት ጋር መፎካከር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ።
የክለቡ ወደ አክሲዮን ለመሸጋገር ከሀገሪቱ ህግ ጋር ማጣጣም
አቶ አብነት፡ ይህ ለክለቡ ታሪካዊ እና ትልቅ ጉዞ ነው፡፡ መንግስት ፖሊሲውን ያሻሽላል ፣ ህጉን ይቀይራል፡፡ ይህን እኛ አናቀውም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ጁነይዲ ቅድም ሲናገሩ እንደሰማችሁት ሀሳቡን ስደግፉ ነበር። ይህ ሀሳብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ አይደለም ለሀገራችንም ቢሆን ትልቅ አማራጭ በመሆኑ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር የሚመለከታቸው አካላት ክለቦች ከመንግስት ድጎማ ተላቀው በራሳቸው አቅም እንዲመሩ መደረግ አለበት፡፡ ክለቦች የራሳቸው ሀብት ካላፈሩ እና ነፃ ሆነው ካልተንቀሳቀሱ ሲወርዱ እየፈረሱ ነገም ሌሎቹ ሲወርዱ የሚፈርሱ ከሆነ የእግር ኳሱ እድገት ምኑ ጋር ነው። እግርኳሱ የተረጋጋ ከመንግስት ድጎማ ፀድቶ ክለቦች ህዝባዊ መሆን አለባቸው፡፡ የዛሬው ቀን ለኢትዮዽያ እግርኳስ አይን መግለጫ ነው። መቼ ወደ ተግባር እንገባለን የሚለውን መጀመርያ ከመንግስት ቁጭ ብለን ጋር መነጋገር አለብን፡፡ ሌላው የደረሰበት ለመድረስ መንግስት ማነቆ መሆን የለበትም፡፡ የነበረው ህግ የድሮ የማህበራት ህግ ነው ፡ ስለዚህ ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ለማምራት ከእነሱ ጋር እናወራለን።
የታገዱትን አባላት ከክለቡ ስለማሰናበት
አቶ ነዋይ፡ የሚገዛን የክለባችን መታደርያ ደንብ ነው፡፡ ይሄንንም በሚገባ መመልከት ያስፈልገናል። መተዳደርያ ደንባችን በግልፅ ማን አባል እንደሆነ እና እንዳልሆነ አስቀምጧል፡፡ ምላዕተ ጉባኤውም በመተዳደርያ ደንባችን መሰረት መሟላቱን አረጋግጦ ተካሂዶል። ስለዚህ ይህንን ጠቅላላ ጉባኤ የጠራነው የአራት ሰዎችን ጉዳይ ወይም እነሱን ለማገድ አይደለም። ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ለአባላቱ ሊያደርስ የሚፈልጋቸው መልክቶች ነበሩ ያንንም በደንብ አድርሰናል። ከዚህ በላይ ለእኛ የጉባኤው ስኬት የምንለው የክለቡን አቅም ለማሳደግ ያቀረብነው ወደ ፊት ልናከናውናቸው የሚገቡ የ5 አመት እቅዳችን ነው። እርግጥ ነው ከጉባኤው እንደተነሳው ልናወያይ በዝርዝር ልንገልፅ ይገባን ነበር። ነገር ግን አጀንዳው ሰፊ በመሆኑ በዝርዝር መወያየት አልቻልንም፡ ይህን ወደ ፊት በስፋት እንመለስበታለን ።
የክለቡ የቦርድ አመራር በአሰልጣኞች ስራ ላይ ጣልቃ ይገባል ስለመባሉ
አቶ አብነት፡ የቦርድ አባላት ከአሰልጣኞች ጋር ምንም ግኑኝነት የላቸውም፡፡ በአሰልጣኞች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ውስጥም ጣልቃ አንገባም ፤ ልንገባም አንችልም፡፡ አሰልጣኝ የምንቀጥረው አምነንበት ነው። ነገር ግን ያለፉትን አመታት ከውጭ የሚመጡ ተጨዋቾች በተመለከተ አሰልጣኞቹ የሚያቀርቡልንን ማፅደቅ ብቻ ነበር የኛ ስራ፡፡ ሆኖም የሚመጡት ተጫዋቾች እዚህ ሀገር ውስጥ ካሉት ተጨዋቾች በምንም ተሽለው ያልተገኙ ተቀያሪ ወንበር የሚቀመጡ ሲሆኑ እኛን ከደጋፊው ጋር እያጋጨ ሲሄዱ አንዳንዶቹ በምን ምክንያት ነው መርጠው ያስገቧቸው በሚል ከዚህ በኋላ ምርጫ ላይ ሄደን ማየት አለብን በሚል የተጫዋች ምርጫ ላይ እየተሳተፍን ነው። ደግሞም ድክመቶችን እየተመለከትን ዝም አንልም ዘንድሮ ክለቡን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ትልቅ እቅድ ስለያዝን ወደ ክለባችን በሚመጡ የሀገር ውስጥ ሆነ የውጭ ተጨዋቾች ምርጫ ላይ ተሳትፎ አድርገናል።
የስታድየም ግንባታ
አቶ አብነት፡ የስታድየሙ ግንባታ ከአክሲዮን ሽግግሩ ጋር ተያይዞ በውስጡ የተካተተ ስራ ነው። በዋናነት ትኩረት የሰጠነው አንዱም የስታድየም ግንባታውን ነው፡፡ የመጀመርያውም ስራችን እሱ እንዲሆን ነው የፈለግነው። ሌሎች የሄድንባቸው አካሄዶች አሉ ፤ መስመር ይዘዋል፡፡ ግን ሳያልቅ መናገር አያስፈልግም በሚል ነው በጠቅላላው ጉባኤ ላይ ሳንገልፅ የቀረነው። ነገር ግን የስታድም ግንባታውን በተመለከተ በዚህ የአክስዮን ኩባንያ ስናቋቁም እሱኑ የመጀመርያ ስራችን አድርገን ለማካተት አስበናል።
የትጥቅ ጉዳዮች
አቶ ዳዊት፡ እስከዛሬ የነበረው ወደ ኋላ መለስ አድርገን ያየነው ከሆነ የትጥቅ አጠቃቀማችን የተዘበራረቀ ነበር። ምክንያቱም ከመልካም ፍቃደኝነት ጋር ተያይዞ በአቶ አብነት ወጪ የሚሸፈን በመሆኑ በየአመቱ ከተለያዩ ድርጅቶች ምርቱ የሚመጣ ስለሆነ ዝብርቅርቅ ያለ ነበር። አሁን ግን ለሁለት አመት የሚቆይ የተሟላ ደረጃውን የጠበቀ ትጥቅ ለማምጣት የተለያዩ ጥናቶች ተጠንተው ለተጫዋቾቹም ለደጋፊዎቹም የሚሆን አንድ ወጥ ትጥቅ እንዲያቀርብልን ማክሮን ከተባለ ትልቅ የጣልያን ድርጅት ጋር ስምምነት ፈፅመናል። የዲዛይን መረጣው ተጠናቆ ወደ ምርት የሚገባ ነው የሚሆነው፡፡ በቀጣይ ባሉት ቀናት ውስጥ ወደ ጨዋታ ከመግባታችን ወይም ከገባን በኋላ ሊሆን ይችላል ሙሉ ትጥቁ ይገባል። ደጋፊውም የማልያው ዋጋው በዛ እያለ ነው፡፡ ያው ጥራት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ታስቦ ነው ከስፖንሰሮች ጋር በመነጋገር ዋጋው ሊቀንስ የሚችልበትን መንገድ እንፈጥራለን።